አርዕስተ ዜና

የክልሉ ኢንተርፕራይዝ ካካሄደው የዘር ብዜት 600 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠብቅ ገለፀ

26 Nov 2016
668 times

አዳማ ህዳር 17/2009 የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ ባለፈው የመኽር ወቅት ካካሄደው የዘር ብዜት ከ600 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር እንደሚጠብቅ አስታወቀ።

በአርሲ ዞን ሙኔሳ ወረዳ ሎሌ እርሻ ልማት ኢንተርፕራይዙ በማካሄድ ላይ ያለው የዘር ብዜት የስራ እንቅስቃሴ ትላንት ተጎብኝቷል።

በመስክ ጉብኝቱ ወቅት የኢንተርፕራይዙ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ከድር ናፎ እንደገለጹት ምርቱ ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀው በምርጥ ዘር ከተሸፈነው 17 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ነው።

ኢንተርፕራይዙ በምርት ዘመኑ ካባዛቸው 19 ዓይነት የሰብል ዝርያዎች መካከል ስንዴ፣ ገብስ፣ ጤፍ፣ እንዲሁም የአገዳ፣ የቅባትና ጥራጥሬ ሰብሎች ይገኙባቸዋል።

የአርሶ አደሩን የዘር ፍላጎት ለማሟላት ኢንተርፕራይዙ በ2008/09 ካባዛው ምርጥ ዘር እስካሁን ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው ምርት ተሰብስቧል።

በአማካይ በሄክታር 40 ኩንታል ምርት መገኘቱን ገልጸው ሳይንሳዊ ዘዴ በመጠቀም ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ምርጥ ዘር በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮች ለማሰራጨት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ተቋሙ ካለው 24 ሺህ ሄክታር ይዞታው ውስጥ 17 ሺህ ሄክታር የሚሆነውን ለአርሶ አደሩ የምርጥ ዘር ብዜት አቅርቦት ልማት እያዋለው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በኢንተርፕራይዙ የአርሲ ዞን ቅርንጫፍ ዳይሬክተር አቶ ውብሸት ፍሱ በበኩላቸው በቅርንጫፉ ስር በሚገኙ አምስት የእርሻ ድርጅቶች በ9 ሺህ 300 ሄክታር መሬት ላይ በተካሄደ የማባዛት ስራ 330 ሺህ ኩንታል የተለያየ ምርጥ ዘር ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነው ምርት ተሰብስቧል ነው ያሉት።

ከሚገኘው ምርት 78 በመቶ የሚሆነው ለአርሶ አደሩ በተማጣጣኝ ዋጋ ለዘር ስራ የሚሰራጭ ይሆናል።

በመስክ ጉብኝቱ ላይ ከተገኙት ሞዴል አርሶ አደሮች መካከል የሙኔሳ ወረዳ አርሶ አደር አለሙ ሻኔ በሰጡት አስተያየት ከኢንተርፕራይዙ ጋር በቅርበት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለፈው መኽር ብቻ በ16 ሄክታር መሬት ላይ ካባዙት የተለያየ ምርጥ ዘር 370 ኩንታል ምርት አግኝተዋል።

ዘንድሮ በማዳበሪያ አቅርቦት በኩል እጥረት እንዳጋጠማቸው ገልጸው በቀጣይ ኢንተርፕራይዙ ከምርጥ ዘር አቅርቦት ባሻገር ማዳበሪያ  ቢያቀርብልን የተሻለ ነው ብለዋል።

አርሶ አደር ገዳ ባቴ በበኩላቸው ከኢንተርፕራይዙ ኦጎልቾ እና ህዳሴ የተባሉ የስንዴ ዝርያዎች በመውሰድ የተሻለ ምርት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን