አርዕስተ ዜና

በምርት ማጠናቀቅ ሂደት የሚያጋጥመውን የጥራት መጓደል ለማስቀረት የቴክኒክ ድጋፍ እየተደረገ ነው Featured

24 Jun 2016
1037 times

አዲስ አበባ ሰኔ 17/2008 በምርት ማጠናቀቅ ሂደት የጥራት መጓደል ችግር እንዳያጋጥም የቴክኒክ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን የማ ጋርመንትና የኬኬ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የስራ ኃላፊዎች ገለፁ።

የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከህንድ ባለሙያዎችና በዘርፉ ከተሰማሩት ባለ ድርሻ አካላት ጋር በጨርቃ ጨርቅ ምርት ማጠናቀቂያ ወቅት በሚፈጠረው የምርት ጥራት ችግር ላይ እየተወያየ ነው።

በውይይቱ የተሳተፉት የማ ጋርመንትና የኬኬ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ኃላፊዎች እንደተናገሩት ኢንስቲትዩቱ በምርት ማጠናቀቅ ሂደት የምርት መጓደልና የአካባቢ ብክለት እንዳይፈጠር ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።  

የማ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የማቅለምና ማጠናቀቅ ስራ አስኪያጅ አቶ ወልደብርሃን መሰለ እንዳሉት በዘርፉ በተለይም በማጠናቀቅ ሂደት የሚያጋጥሙ የጥራት ችግሮችን ለመፍታት ፋብሪካው ከኢንስቲትዩቱ ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።

ለፋብሪካው ከደንበኞች የሚቀርቡትን የጥራት ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ለመመለስ ኢንስቲትዩቱ በሚያዘጋጃቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ላይ በመሳተፍ ልምድ በመቅሰም ላይ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።

የሰራተኛውን አቅም በማሳደግ ችግሮቹን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

ከኬኬ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ የመጡት አቶ አይችሉም ክፍሌ ፋብሪካቸው የሱፍ ክር በሚያቀልምበት ወቅት የጥራት ችግር እንዳያጋጥመው የሙያ ድጋፍ እየተደረገለት ነው።

የዓለም አቀፍ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎችን ተሞክሮ በመቀመር ኢንስቲትዩቱ እያደረገላቸው ያለው የቴክኒክ ድጋፍ ውጤታማ እንዳደረጋቸውና ከፋብሪካው የሚወጡ የፍሳሽ ተረፈ ምርቶችን መልሶ ለመጠቀም እንዳገዛቸው ተናግረዋል።

በኢንስቲትዩት የማጠናቀቂያ ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ ፍቅር ተስፋ እንዳሉት፣የጨርቃጨርቅና አልባሳት የምርት ሂደት ረጅም ሰንሰለት ያለው ቢሆንም፤ በተለይ በማቅለምና በማተም ጊዜ የጥራት መጓደል ያጋጥማል።

ኢንስቲትዩቱ በምርት ማጠናቀቅ ሂደት ወቅት የሚያጋጥመውን የጥራት መጓደል ችግር ለመፍታትና ተረፈ ምርቱም በአግባቡ እንዲታከም ከፋብሪካዎች ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው።

ኢንስቲትዩቱ የዘርፉ ችግሮችን ለመፍታት በየሶስት ወራት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንደሚያዘጋጅና ከህንድ ፋብሪካዎች ጋር በቅንጅት በመስራት ተቋማዊ አቅሙን እየገነባ መሆኑን ነው የገለጹት።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ እንዳሉት የአብዛኛዎቹን የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች የማጠናቀቂያ ምርት ጥራት መጓደል ችግር ለመፍታት ከጥጥ ልማትና ግብይት ጀምሮ ጥንቃቄ እንዲደረግ ለፋብሪካዎች የቴክኒክና የክህሎት ድጋፍ እየተደረገ ነው።

በዘርፉ የሚያጋጥመውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ችግር ለመፍታትም ከዩኒቨርሲቲዎችና ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት በዘርፉ የሚያጋጥሙትን የጥራት ችግሮች ለመፍታትና ዓለም አቀፍ የገበያ ተቀባይነትን ለማግኘት ታዋቂ ከሆኑ የህንድ ፋብሪካዎች ተሞክሮ በመውሰድ ለአገር ውስጥ አምራቾች ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እየተዘጋጁ  ነው።

በአገሪቷ የሚገኙት 150 በመካከለኛና ከፍተኛ የማምረት ሂደት ውስጥ ያሉ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች 60ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን