አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 444

በድሬደዋ የወጣቶችን የስፖርት ተሳትፎ ለማጠናከር ይሰራል---የአስተዳደሩ ከንቲባ

26 Jan 2016
3633 times

ድሬዳዋ ጥር 16/2008  በድሬደዋ የሴቶችና ወጣቶችን የስፖርት ተሣትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ ተግባራት እንደሚከናወኑ የከተማዋ አስተዳደር ከንቲባ ገለጹ፡፡

በመጪው ወር ሃዋሳ በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ጨዋታ ላይ ድሬደዋን  የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ ሲካሄድ የቆየው አራተኛው የመላው ድሬደዋ የልዩ ልዩ ስፖርት ውድድር ዛሬ ተጠናቋል

የዕለቱ የክብር እንግዳ የድሬዳዋ አሰተዳደር ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ዑስማን ከሌሎች የስራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን ለአሸናፊ ቡድኖች የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ከሰጡ በኋላ እንደገለጹት ለሶስት ሣምንታት የተካሄደው ውድድር የድሬደዋን የስፖርት እንቅስቃሴ አነቃቅቷል፣ የስፖርቱን ህዝባዊ መሠረት ለማጠናከርም አግዟል፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ሴቶችና ወጣቶች በስፖርቱ ያላቸውን ተሣትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ የሚያጠናክሩ ተግባራት እንደሚከናወኑም ገልጸዋል፡፡

በየስፖርት ዓይነቱ የማዘውተሪያ ስፍራዎችን የመገንባቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያመለከቱት ከንቲባው ለመላው የኢትዮጵያ ጨዋታዎች የተመረጡት ስፖርተኞች የድሬዳዋን ገጽታ በመገንባትና የስፖርት ቤተሰቡ የሚጠብቀውን ውጤት ለማስመዝገብ ጠንክረው እንዲሰሩም አሳስበዋል፡፡

የአስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ከዲር ጁሃር በበኩላቸው " ውድድሩ በመጪው ወር ሃዋሳ  በሚካሄደው ሀገር አቀፍ ጨዋታ ላይ ድሬደዋን የሚወክሉ ተተኪዎች ከማስገኘቱ በላይ  ስፖርተኞቹ ቅንጅታቸውን  አጠናክረው በአንድነት ውጤታማ ለመሆን አነቃቅቷቸዋል "ብለዋል፡፡

ባለሀብቱ፣ የስፖርት ቤተሰቡ፣ መንግስትና ሌሎች የስፖርት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ከሠሩ ሀገርን በዓለም አደባባይ  ማስጠራት የሚችሉ ስፖርተኞችን ማፍራት እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

ከዘጠኙ የከተማዋ አስተዳደር ቀበሌዎች ዜሮ ሁለት ቀበሌ የመላው ድሬደዋ አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን ዜሮ ሶስት እና ዜሮ አምስት ቀበሌዎች ደግሞ በቅደም ተከተል  ሁለተኛና ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡

የመላ ድሬዳዋ ስፖርት ውድድር  18 የሰፖርት ዓይነቶች አካትቷል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን