አርዕስተ ዜና

በኢትዮጵያ አምስት ቋሚ 'ፕላኔተሪየሞች' ይገነባሉ - የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ

አዲስ አበባ የካቲት 24/2010 በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ አምስት ቋሚ 'ፕላኔተሪየሞች' እንደሚገነቡ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ አስታወቀ።

ፕላኔተሪየም በምድር ላይ ሆኖ የህዋ አካላት የሆኑት ከዋክብት፣ ጋላክሲዎችና ፕላኔቶች የሚያደርጉትን አጠቃላይ እንቅስቃሴ መመልከት የሚቻልበት ቦታ ነው።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ለሁለት ቀናት የሚያካሂደው 12ኛው ጠቅላላ ጉባዔው ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተጀምሯል።

የሶሳይቲው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብነት እዝራ ለኢዜአ እንደገለጹት በተጠቀሱት ዓመታት አምስት ቋሚ 'ፕላኔተሪየሞች' በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይገነባሉ።

የስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲው ቦርድ በነሐሴ 2009 ዓ.ም ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት ለ'ፕላኔተሪየሙ' ግንባታ የመጀመሪያ ምዕራፍ የሆነው የፕሮጀክት ጥናት በጃፓን፣ ስፔንና እንግሊዝ የፕላኔታሪየም ተቋማት መካሄዱን ገልፀዋል።

ከጥናቱ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ የሚሆኑ ተሞክሮዎችና እውቀት እንደተገኘም አመልክተዋል።

ጥናቱ በተካሄደባቸው አገራት ከሚገኙ ተቋማት ጋር ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር ከመቻሉ ባሻገር ስለ 'ፕላኔተሪየም' ምንነት ተጨባጭ እውቀት መቅሰም መቻሉንም ነው አቶ አብነት ያብራሩት።

በተጨማሪም ለ'ፕላኔተሪየሞቹ' ግንባታ እውን መሆን የሚያስፈልጉ ወሳኝ ግብዓቶችና የምህንድስና ስራዎችንም ለማወቅ ተችሏል።

በጥናቱ መሰረት የቋሚ 'ፕላኔተሪየሞች' ግንባታው ከሶስት እስከ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ መጠናቀቅ እንዳለበትና ለዚሁ የሚሆን ገንዘብም ከአገር ውስጥና ከውጭ አገራት ማሰባሰብ እንደሚያስፈልግ መታወቁን ገልጸዋል።

አንድ ቋሚ 'ፕላኔተሪየም' ለመገንባት 200 ሚሊዮን ብር እንደሚፈጅና ይህም ከስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲው አቅም በላይ በመሆኑ ለመንግስትና ለውጭ አገራት ድርጅቶች ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአንድ ዓመት ሁለት ተንቀሳቃሽ 'ፕላኔተሪየሞችን' ገዝቶ ማስገባትና ስራ ላይ ማዋል የሚቻልበት ሁኔታ እየተመቻቸ መሆኑንም ነው አቶ አብነት የተናገሩት።

ለዚህም የሚያስፈልገውን የሁለት ሚሊዮን 340 ሺህ ብር የሀብት ማሰባሰብ ስራ በስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲው እየተከናወነ ነው ብለዋል።

የሀብት ማሳበሰብ ስራው ከተከናወነ በኋላ ለግንባታው የሚያስፈልገው መሬት ጥያቄ ለአዲስ አበባ አስተዳደር እንደሚቀርብ ተናግረዋል።

የራስን 'ፕላኔተሪየም' መገንባት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ የሚያስወጣ ቢሆንም፤ አገሪቷ ሳተላይት ለመግዛት ከምታወጣው ወጪ በላይ እንደማይጠይቅ ነው ያስረዱት።

በአሁኑ ወቅት የህዋ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ፕሮግራም በመጠቀም ድህነትን አሸንፎ ብልጽግና ማምጣት እንደሚያስችል መታመኑ በዘርፉ ከታዩ ትልቅ የአመለካከት ለውጦች ውስጥ ዋነኛው እንደሆነም ነው አቶ አብነት የተናገሩት።

በህብረተሰቡ ዘንድ ኢትዮጵያ በስፔስ ሳይንስ አሳካቸዋለሁ ብላ ያቀደቻቸውን ሃሳቦች እውን ታደርጋለች የሚል የይቻላል እምነት እያደገ መምጣቱንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ በአሁኑ ጉባዔው የስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲውን ቅርጫፍ ጽህፈት ቤቶች የ2009 ዓ.ም በጀት ዓመት ሪፖርት የሚያደምጥ ሲሆን የዘርፉ ተመራማሪዎች የህዋ ሳይንስ ጥናትና ጽሁፍ እንደሚያቀርቡም የወጣው መርሃ ግብር ያሳያል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ሐምሌ 10 ቀን 1996 ዓ.ም በ47 አባላት የተቋቋመ ሲሆን አሁን ከ10 ሺህ በላይ አባላትን አፍርቷል።

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን