አርዕስተ ዜና

አገራዊ የመረጃ ቋት ተዘጋጀ

አዲስ አበባ የካቲት 22/2010 የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አዲስ አገራዊ የዲጂታል የመረጃ ቋት አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን አስታወቀ።

የመረጃ ቋቱ የተዘጋጀው ባለፉት አራት ዓመታት ሲሆን፤ አሁን ላይ ስራው ተጠናቆ ወደ ትግበራ መግባቱንም የሚኒስቴሩ የመረጃ ማዕከል አስታውቋል።

ይህም መረጃ የማግኘት ችግሮችን የሚያቃልልና ለዚሁ ሲባል የሚባክኑ ሃብቶችን የሚያስቀር መሆኑ ተገልጿል።

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍስሐ ይታገሱ እንዳሉት፤ የመረጃ ቋቱ የመማር ማስተማር ሂደትን ጨምሮ የተለያዩ ጥናቶች ሲካሔዱ የሚያጋጥሙ የመረጃ እጥረቶችን ይፈታል።

በተጨማሪም ተቋማት በህትመትና በድረ-ገጽ በቀጥታ ለሚያደርጓቸው የመፃህፍት ግዢዎች የሚያወጡትን በርካታ ገንዘብ ለመቀነስም እንደሚያስችል ነው የጠቆሙት።

እንዲሁም ተማሪዎችና ተመራማሪዎች ለማግኘት የሚቸገሩባቸውንና ውድ የሆነ ዋጋ ያላቸውን ጥናቶችንና መፃህፍት በነፃ እንዲያገኙ በማድረግ የተሻለ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ያደርጋል።

በተጨማሪም በአሁን ወቅት እንደ ችግር የሚነሳውን "የተመሳሳይ የጥናት ስራና ፅሁፍ ስርቆትም ያስቀራል" ነው የተባለው።

የመረጃ ቋቱ ከትምህርት ተቋማት በተጨማሪ ለፖሊሲ አውጭዎችና ውሳኔ ሰጪ አካላትም አስፋላጊ የሆኑ ግብዓቶችን በማቅረብ ረገድ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

እርሳቸው እንዳሉትም አሁን ላይ ማንኛውም ሰው "library.stic.et" በሚለው ድረ ገፅ በመግባት የተለያዩ መፃህፍትን፣ አርቲክሎችን፣ የምርምር ጽሁፎችን፣ ህጎችን ፣ ሜጋ ፕሮጀክቶችንና ዓለማአቀፍ ስምምነቶችን በኢንተርኔት ማግኘት እንደሚቻል ገልፀዋል።

ይህንኑ አገልግሎት ለማግኝት የኔትወርክ መቆራረጥ ሊገጥም ስለሚችል ተጠቃሚዎች ያለኢንተርኔት ግንኙነት ሊያስጠቅም የሚችል አፕሌክሽንን በስልካቸው ላይ በመጫን መጠቀም እንደሚችሉ አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ ይፋ ባደረገው ቋት ውስጥ ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን በላይ መረጃዎች የሚገኙ ሲሆን፤ ከ57 ሺህ በላይ መፃህፍትም እንደሚገኙ ነው ያመለከቱት።

ዲጂታል የመረጃ ቋቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚሰራ እንደሆነም ነው ለማወቅ የተቻለው።

በአሁኑ ወቅት ስራውን ከዚህ በላቀ ደረጃ ለማቀላጠፍና ሁሉንም ተቋማት ለማስተሳሰር በሚደረገው ሂደት አንዳንድ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ፈቃደኝነት አለማሳየታቸው እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ዲጂታል የመረጃ ቋት በየትኛውም ቦታ ሆነው በርካታ የሆኑ ሰዎች በአንድ ወቅት መረጃ ለማግኝት የሚያስችል የቤተ መጽሐፍት ስርዓት ነው።

Last modified on Friday, 02 March 2018 00:46
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን