አርዕስተ ዜና

በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ባለድርሻ አካላትን የሚያስተሳስር ቴክኖሎጂ ሊተገበር ነው

አዲስ አበባ ጥር 29/2010 በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ባለድርሻ አካላትን የሚያስተሳስር "ቢውልዲንግ ኢንፎርሜሽን ሞዴል" የተሰኘ ቴክኖሎጂ ለመተግበር የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተነገረ።

 የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂውን ተደራሽነት ለማስፋት ለ20 የዘርፉ ባለሙያዎች የአሰልጣኝነት ስልጠና እየሰጠና የፖሊሲ ዝግጅትም እያደረገ መሆኑን ገልጿል።

 ከአሜሪካ የመነጨው ይህ ቴክኖሎጂ በእንግሊዝና በሩቅ ምስራቅ አገሮች በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑም ተነግሯል።

 ቴክኖሎጂው የግንባታው ባለቤት፣ የስራ ተቋራጩ፣ አማካሪውና ግብዓት አቅራቢዎች በቅንጅት እንዲሰሩ የሚያስችልም ነው።

 የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋ አሻ ለኢዜአ እንደገለጹት ቴክኖሎጂው በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የአንድ ህንጻ ግንባታ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ በቅንጅትና በመናበብ እንዲሰሩ ያደርጋል። 

 ከግንባታ በፊት ህንጻው ምን እንደሚመስል፣ የሚያስፈልጉት የግብዓት ዓይነቶች፣ የኤሌክትሪክ፣ የፍሳሽ መስመሮችና ለዚሁ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን በቅድሚያ በመለየትና በማሳየት በግንባታ ሂደት የሚከሰትን አላስፈላጊ ወጪ ያስቀራል፤ ጊዜም ይቆጥባል።

 በግንባታ ወቅት በህንጻው ላይ የዋጋ፣ የዲዛይንና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለውጥ ቢከሰት ባለድርሻ አካላቱ በተመሳሳይ ጊዜ ስለ ለውጡ እንዲያውቁ ማድረግም ያስችላል እንደ ዶክተር አረጋ ገለፃ።

 ይህም አንድ የኪነ-ህንጻ ባለሙያ በሚሰራው ህንጻ ላይ የተወሰነ ለውጥ ሲያደርግ ለውጡን ለህንጻው ባለቤትና ለኮንትራክተሩ በማሳየት የሚፈጀውን ገንዘብና ጊዜ ለማወቅ ይረዳል ነው ያሉት።

 የቴክኖሎጂውን ተደራሽነት ለማስፋት የአሰልጣኞች ስልጠና በመውሰድ ያሉ ባለሙያዎች ስልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ ሌሎችን በማሰልጠን ቴክኖሎጂው ወደ ኮንስትራክሽን ዘርፉ የበለጠ እንዲሰርፅ የማድረግ ሥራ ይሰራሉም ብለዋል።

 በመንግስት በኩል ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ከ10 እስከ 20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በሚኖራቸው ግንባታዎች ላይ ቴክኖሎጂውን ለመተግበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ዶክተር አረጋ ገልጸዋል።

 በዚህም በዘርፉ የሚስተዋሉትን የሙስናና ሌሎች ብልሹ አሰራሮችን ማስወገድ ይቻላል የሚል እምነት መኖሩን ተናግረዋል።

 የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ምርጥ ተሞክሮዎችን፣ ወጪ ቆጣቢና የተሻሻሉ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ቴክኖሎጂዎችን አጠቃቀም ለማሻሻል የተቋቋመ ተቋም ነው።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን