አርዕስተ ዜና

የአፍሪካ የካይዘን የስልጠና ልህቀት ማዕከል በኢትዮጵያ ሊገነባ ነው

ባህርዳር ጥር 29/2010 የአፍሪካ የካይዘን የስልጠና ልህቀት ማዕከል ግንባታ በቅርቡ  ለማስጀመር ዝግጅቱ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

በኢንስቲትዩቱ የአቅም ግንባታ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ለቤዛ አለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት ማዕከሉ የሚገነባው በአዲስ አበባ ሳር ቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ20 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው።

ግንባታውን ለማስጀመር የሚያስችሉት የቦታ ዝግጅት፣ የግንባታ ዲዛይንና ጥናቶች መጠናቀቃቸውንም ተናግረዋል።

"የስልጠና ማዕከሉ በውስጡ የሰልጣኞች መኝታ ክፍሎች፣ የአስተዳደር ቢሮዎች፣ የመማሪያና  ሌሎችንም የመገልገያዎች ክፍሎችን የሚያካትት ነው" ብለዋል።

የግንባታው ወጪው ከጃፓን መንግስት በተደረገ ድጋፍ እንደሚሸፈን ያመለከቱት አቶ ለቤዛ እስከ 400 ሚሊዮን ብር ድረስ ወጪ እንደሚጠይቅ ጠቅሰዋል።

ግንባታው እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2018 ውስጥ እንደሚጀመር የሚጠበቅ ሲሆን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ማሰልጠን ይጀምራል ተብሏል።

አቶ ለቤዛ  እንዳሉት የልህቀት ማዕከሉ ስራ ሲጀምር ከኢትዮጵያና ከሌሎች  የአፍሪካ ሃገራት የሚመጡ ሰልጣኞችን ተቀብሎ የካይዘን ፍልስፍናን ያስተምራል።

የማዕከሉ መገንባት በኢትዮጵያ ከመጀመሪያ ወደ ሁለተኛ ደረጃ እየተሸጋገረ የሚገኘውን ካይዘን በተሻለ ጥራት ለመተግበር ተጨማሪ አቅም ይፈጥራል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ካይዘንን በፋብሪካዎችና በተለያዩ ተቋማት በመተግበር ከሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ከብክነት ማዳን እንደተቻለም ተመለክቷል።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን