አርዕስተ ዜና

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን 28 የባዮ ጋዝ ማብላያ ተቋማት አገልግሎት መስጠት ጀመሩ

ጎንደር ሚያዚያ 5/2010 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት 28 የባዮ ጋዝ ማብላያ ተቋማት ተገንብተው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን የዞኑ ውሃ መስኖና ኢነርጂ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ጌታቸው መስፍን ለኢዜአ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ 454 የባዮ ጋዝ  ማብላያ ተቋማት ለመገንባት ታቅዶ የ65ቱ ሥራቸው ተጀምሯል።

"ግንባታቸው ከተጀመሩት ማብላያዎች ውስጥ 28ቱ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል" ያሉት ኃላፊው የ37ቱ ተቋማት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀሪዎቹን የማብላያ ተቋማት ግንባታ ለማስጀመር የቦታ መረጣ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።

የማብላያ ተቋማቱ በ13 ወረዳዎች የሚገነቡ መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።

ሀላፊው እንዳሉት የማብላያ ተቋማቱ እያንዳንዳቸው ከስድስት እስከ ስምንት ሜትር ኪዮብ የከብቶች እዳሪ ማጠራቀም የሚያስችል ጉድጓድ አላቸው። 

"የማብለያ ተቋማቱ የኤሌትሪክ አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው የገጠር ክፍሎች በአካባቢው ቁሳቁስና በቀላል ወጪ አማራጭ የኃይል ምንጭ ለማስፋፋት ያስችላሉ" ብለዋል፡፡

"ለአንድ የባዮጋዝ ማብላያ ግንባታ 5 ሺህ ብር ይጠይቃል" ያሉት አቶ ጌታቸው፥ ለተቋማቱ ግንባታ የሚያስፈልገው ወጭ በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ እንደሚሸፈን ጠቁመዋል።

የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎቹ አርሶ አደር ማሩ ተስፋሁንና ወይዘሮ ጥሩዬ ጋሻው በሰጡት አስተያየት በማብላያ ጉድጋዱ የሚመነጨውን ኃይል በመጠቀም በቤት ውስጥ ምግብ ማብሰልና መብራት መጠቀም ጀመረዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ  ባዮ ጋዝ መጠቀም በመጀመራቸው ወጪ እንደቀነሰላቸውና በእንጨት ጭስ ምክንያት የሚያጋጥማቸው የዓይን ጉዳት እንደቀረላቸው ተናግረዋል።

በአለፋ ወረዳ የእሰይ ደብር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አይሸሹም ቸርነት በበኩላቸው ለኃይል ማመንጫነት የዋለውን ተረፈ ምርት፥ በማሳቸው ውስጥ በመጨመር ለምርት ማሳደጊያነት በመጠቀማቸው ለማዳበሪያ ግዥ የሚያወጡት ወጭ እንደቀነሰላቸው ገልፀዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ባለፉት አራት ዓመታት ከ800 በላይ አርሶ አደሮች የባዮ ጋዝ ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

 

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን