አርዕስተ ዜና

ከምርምር ማዕከሉ ያገኙት ምርጥ ዘር ለውጤት እንዳበቃቸው አርሶ አደሮች ገለጹ

03 Jan 2018
768 times

መቀሌ ታህሳስ 25/2010 ከመቀሌ ግብርና ምርምር ማዕከል የሚያገኙትን የቅመማ ቅመም ምርጥ ዘር በመጠቀም የተሻለ ምርታማ መሆናቸውን አርሶ አደሮች ገለጹ።

ማዕከሉ በምርምር ያገኛቸውን ሶስት አይነት የቅመማ ቅመም ዝርያዎች ለአርሶ አደሩ የማላመድና የማስተዋወቅ ስራ እያከናወነ ይገኛል።

በትግራይ ማእከላዊ ዞን የደጋ ተምቤን ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ሐጎስ ብርሃነ እንደገለጹት በመሰኖ እርሻቸው ለረጅም ዓመታት ሽንብራ በማልማት ያገኙት የነበረው ገቢ ዝቅተኛ ነበር።

አሁን ግን ምርጥ የቅመማ ቅመም ዘር ተጠቃሚ በመሆናቸው በአንድ ዙር ካለሙት ቅመማቅመም 30 ሺህ ብር በማግኘታቸው ገቢያቸውን ማሳደጋቸውን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የሚጠቀሙበት ዝርያ በቀላሉ በተባይና በበሽታ ስለሚጠቃም በሔክታር ከአምስት ኩንታል እንደማይበልጥ ገልጸው ከተሻሻለው ምርጥ ዘር በሔክታር 20 ኩንታል ጥቁርና ነጭአዝሙድ እንደሚያገኙ አስረድተዋል።

"ከዚህ በተጨማሪም ፍሬው ወፍራም ፣በጣም ተመራጭ በመሆኑ ለዘርም ስለሚፈለግ አንዱን ኪሎ በ120 ብር በመሸጥ ተጠቃሚ ሆነናል" ብለዋል።

በየዓመቱ መስኖ ግብርና በቆሎ በማልማት ሲጠቀሙ የቆዩት አርሶ አደር አብርሃ ጎድፋይ በበኩላቸው ከአካባቢያቸው የአየር ጸባይ ጋር የሚስማማ የአብሽ ዝርያ ማልማት ከጀመሩ ሁለት ዓመት ሆኗቸዋል።

በሩብ ሄክታር ማሳቸው ላይ ይሔንኑ ዝርያ ያለሙት አርሶ አደሩ ቀደም ሲል በቆሎ እሸት ሽጠው ከሚያገኙት ገቢ  ከአምስት እጥፍ በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

"በአካባቢያችን ቅመማ ቅመም በኩታ ገጠም ለማልማት ሁሉም መስኖ ተጠቃሚ አርሶ አደር አዋጭነቱን ስላወቀው በየማሳው ዘርቶ እያለማ ነው " ብለዋል።

አርሶ አደሩ በሩብ ሄክታር መሬት ከዘሩት አብሽ 12 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውንና ይሔም በገንዘብ ሲሰላ ከ20ሺህ ብር በላይ እንደሚሆን ተናግረዋል።

በወረዳው የአንድነት ቀበሌ የኤክስቴንሽን ባለሙያ አቶ አብርሃ ታመነ እንደገለጹት ቀደም ባሉት ዓመታት በመስኖ ልማት የሚበቅለው የበቆሎእሸት፣ቲማቲም፣ሽንብራና የተለያዩ አትክልቶች ብቻ ነበሩ።

አሁን አብዘኞቹ አርሶ አደሮች በገበያ ተፈላጊ መሆኑና አዋጭነቱ አውቀው ወደ ቅመማ ቅመም አዝርእት በመዞር በስፋት እያለሙት እንደሚገኙ ተናግረዋል።

"በአንድነት ቀበሌ ብቻ በመስኖ እየለማ ካለው 650 ሄክታር መሬት ውስጥ 200 ያህሉን ቅመማቅመም ፣አብሽና ነጭ ሸንኩርት አፈራርቀው አያለሙት ነው" ብለዋል ።

በመቀሌ ግብርና ምርምር ማዕከል የመስኖ ተመራማሪው አቶ ታደሰ አባዲ እንደገለጹት ማዕከሉ በምርምር ያገኛቸውን ምርጥ ዘሮች ለአርሶ አደሩ በማከፋፈል ምርታማነቱን ለማሻሻል እየሰራ ይገኛል።

ቀደም ባሉት ዓመታት የቅመማ ቅመም እርሻ በክልሉ በስፋት ባለመታወቁ የአካባቢው የአየር ጸባይ አይስማማውም በሚል አርሶ አደሩ እንደማይሳተፍበት ተናግረዋል።

ከክልሉ ስነ-ምህዳር ጋር የሚስማሙ 120 የአብሽ፤ነጭና ጥቁር አዝሙድ ዝርያዎችን በማስመጣት ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምርና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በተደረገ ምርምር የተሻሉ ዝርያዎችን በማውጣት በአርሶ አደሮች እንዲባዛ ተደርጓል።

"ዝርያዎችም በተመራማሪዎችና ሞዴል አርሶ አደሮች ተባዝተው እንዲስፋፉ ተደርገው ጥቅም ላይ በመዋላቸው በሄክታር ከ16 እስከ 20ኩንታል ምርት እየሰጡ ናቸው " ብለዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ