አርዕስተ ዜና

በሀገሪቱ የህዋ ሳይንስ ቴክኖሎጂን በማሳደግ ልማቱን እንዲደግፍ በትኩረት እየተሰራ ነው ---አቶ ተፈራ ዋልዋ Featured

02 Jan 2018
857 times

 ጎባ ታህሳስ 24/2010 በሀገሪቱ የህዋ ሳይንስ ቴክኖሎጂን በማሳደግ ልማቱን እንዲደግፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን  የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ የበላይ ጠባቂ አቶ ተፈራ ዋልዋ ገለጹ፡፡

" የህዋ ሳይንስ ለሀገሪቱ ዘላቄታዊ ልማት !" በሚል መሪ ሀሳብ ሶሳይቲው ከመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር ያዘጋጀው አውደ ጥናት ዛሬ በባሌ ሮቤ ከተማ ተካሄዷል።

የሶሳይቲ የበላይ ጠባቂ አቶ ተፈራ ዋልዋ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ሀገሪቱ ቀደም ሲል በዘርፉ ያልነበራት ስልጠና ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ፣ በባህር ዳርና በጂማ ዩኒቨርሲቲዎች በሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ማስተማር ጀምራለች፡፡

" በሀገሪቱ የህዋ ሳይንስ የምርምር ማዕከልና ማሰልጠኛ ተቋም ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩም ዘርፉን ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ማሳያ ነው " ብለዋል።

በህዋ ሳይንስ ዘርፍ ምርምር ለሀገሪቱ እንዲሁም ለዓለም ጥቅም የሚሰጡ የተፈጥሮ ፀጋዎች በጥናት መለየታቸውንም ጠቅሰዋል።

በዘርፉ የሰለጠና ባለሙያ ለማፍራት በአሁኑ ወቅት በእንጦጦ የምርምር ስልጠና ማዕከል 43 ተማሪዎችን በሶስተኛ ዲግሪ መርሓ ግብር ትምህርት በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ በመስኩ የተሻለ ደረጃ ላይ ለመድረስ  ስትራቴጂያዊ እቅድ ነድፋ እየተንቀሳቀሰች ነው፡፡

አቶ ተፈራ በቀጣይም ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት፣ምቹ የሆነውን የአየር ንብረት በአግባቡ መጠቀም፣ዓለም አቀፍ ትብብርን ማስፋትና ማጠናከር በልዩ ትኩረት የሚሰራበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቱ  እየተከናወነ ያለውን የስፔስ ሳይንስ እንደ ቅንጦት የሚቆጥሩ አካላት እንዳሉ  ጠቁመዋል፡፡

ይህንን የአመለካከት ችግር ለማስወገድ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግና ሀገራዊ የህዋ ሳይንስን በማሳደግ ልማቱን እንዲደግፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተካሄደው አውደ ጥናትም  ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ የሰለጠና የሰው ኃይል በማፍራት የህዋ ሳይንስን እንዲደግፍ ከማድረግ ባሻገር የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ እንደሚያበረክት አመልክተዋል፡፡

በመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የምርምር ፤ ማህበረሰባዊ አገልግሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ስሜነህ ቤሴ በበኩላቸው የአውደ ጥናቱ ዓላማ የህዋ ሳይንስ ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ዕድገት ያለው ጠቀሜታ ከነባሪዊ ሁኔታዎች ጋር በተገናዘባ መልኩ በመወያየት  የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዶክተር ስሜነህ እንዳሉት የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግቦችን ለማሳካት ሳይንስና ቴክኖሎጂ በተለይ የህዋ ሳይንስ እውቀትን እንደ ምርኩዝ ይዞ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡

" የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች፤ መምህራንና ማህበረሰብ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆኑ ቴክኖሎጂ ፈጣሪ ለመሆን መጣር አለበቸው "ብለዋል ፡፡

ዩኒቨርሲቲው የስፔስ ሳይንስ ሶሳይትን በቅርቡ በማቋቋም በ2020 ዓ.ም የራሱን የህዋ ሳይንስ ጣቢያ ለማቋቋም ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ዶክተር ስሜነህ ጠቁመዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ በ1996 ዓ.ም በ47 አባላት የተቋቋመ ሲሆን አሁን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አባላት እንዳሉት ተመላክቷል፡፡

የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ መምህር ዶክተር አሸብር መስፍን በአውደ ጥናቱ የህዋ ሳይንስ ለሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ያለውን ሚና መገንዘባቸውን ተናግረዋል ፡፡

ለአንድ ቀን በተካሄደው አውደ ጥናት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና መምህራን፣ ከባሌ ዞን  የተለያዩ የመንግስት  መስሪያ ቤቶች የተወጣጡና ሌሎችም  ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡  

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ