አርዕስተ ዜና

የአዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የግብርና ምርቶችን በባለቤትነት ማስመዝገብ ላይ ክፍተት አለበት ተባለ

አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2010 የግብርና ምርቶችን በባለቤትነት ማስመዝገብ ካልተቻለ ኢትዮጵያ በዘርፉ ልታገኝ የሚገባትን እድገትና ጥቅም ልታጣ እንደምትችል ተጠቆመ።

ይህ የተገለፀው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሳይንስ፣ መገናኛና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤትን የዘጠኝ ወራት ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ነው።

ኢትዮጵያ በሌሎች አገሮች የሌሉ የእህል፣ የእፅዋትና የእንስሳት ሃብት ቢኖራትም በባለቤትነት ባለመመዝገባቸው አገሪቱ ማግኘት የምትችለውን ጥቅም እያሳጣት ነው ብሏል ቆሚ ኮሚቴው ።

በቅርቡ አገሪቱ ያጣችው የጤፍ ባለቤትነት የግብርና ምርቶች በባለቤትነት የማስመዝገብ ክፍተት ስለመኖሩ ማሳያ ነው ተብሏል ።

የአእምሯዊ ንብረት ፅህፈት ቤት በዕቅድ አፈጻጸሙ የግብርና ምርቶችን ባለቤትነት የማስመዝገብ ሂደት ክፍተት የታየበት ነው።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው መለስ እንደገለፁት፤ የግብርና ምርት የሆነውን ጤፍ ቀደም ሲል በባለቤትነት በአገር ውስጥና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ማስመዝገብ ባለመቻሉ ሌሎች ተቋማት የባለቤትነት መብቱን ሊወስዱ ችለዋል።

አሁንም የግብርና ምርት የሆኑ የተለያዩ የቡና ምርቶች፣ የጤፍና የእዕፅዋት ዝርያዎች ቢኖሩም ምዝገባ እንዳልተደረገላቸው ሰብሳቢው ጠቁመዋል።

ግብርና መር የሆነውን የኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠንና ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ የአገሪቱን የግብርና ውጤቶች ባለቤትነት ማስጠበቅ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ነው ቋሚ ኮሚቴው ያሳሰበው።

ተቋሙ በበኩሉ የነዚህን ምርቶች ባለቤትነት ለማረጋገጥ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም አንዳንድ የህግ ማዕቀፎች አለመሟላትና ለአሰራር ምቹ አለመሆን ችግር እየፈጠሩ እንደሆነ አስታውቋል።

ችግሩን ለመቅረፍም የፖሊሲና አዋጆች ረቂቅ አዘጋጅቶ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት መላኩን ገልጿል።

የተቋሙ ተወካይ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤርምያስ የማነብርሃን እንዳሉትም የግብርና ምርቶችን ባለቤትነት ለማረጋገጥና የሚገኘውንም ጥቅም ለማሳደግ ከማሳ ጀምሮ ያሉ ሂደቶች ከታሪካዊ ዳራቸው ጭምር የማጥናት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ሂደትም በቅርቡ የተለያየ ዝርያ ያላቸው የቡና፣ የጤፍ፣ የጤና አዳምና የጭሳጭስ እፅዋት ምዝገባ በቅርቡ ይካሄዳል ብለዋል።

 

Last modified on Wednesday, 11 April 2018 21:40
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን