አርዕስተ ዜና

ኤሌክትሪክን ለሁሉም ለማድረስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና የጎላ ነው...የውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር Featured

30 Dec 2017
896 times

መቀሌ ታህሳስ 21/2010 በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ሃገር አቀፍ ተደራሽነት ሙሉ በሙሉ ለማሳካት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና የጎላ መሆኑን የውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በዘርፉ የሚካሄድ  ምርምር ፣ቴክኖሎጂ የማመንጨትና የሙከራ ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ ለመፈጸም መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው ሀገር አቀፍ አውደ ጥናት ዛሬ መቀሌ ላይ ተካሂዷል።

በሚኒስቴሩ የኤነርጂ ጥናትና ልማት ከፍተኛ ባለሞያ አቶ ይሔይስ እሸቱ በአውደ ጥናቱ ላይ እንደገለጹት እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2025 በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉንም ቤተስብ የኤነርጂ ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተዘጋጅቷል።

እቅዱን ተግባራዊ በማድረግ በኩል ከፍተኛ የአቅም ችግር መኖሩን አስረድተው በዓመት ለሚሊዮኖች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማድረስ ቢጠበቅም አፈጻጸሙ ከመቶ ሺህዎች እንዳልዘለለ ተናግረዋል።

"እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የሁሉም ባለደርሻ አካላት  በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እውቀት ግብዓትና ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል።

እንዲሁም ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር የራቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን በአማራጭ የሀይል ምንጮች ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በምርምር የተደገፈ የኤነርጂ ቴክኖሎጂ  ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቅርቡ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት በአገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ቤተሰቦች ከ20 በመቶ ወደ 33 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጽዋል።

በሚቀጥሉት ሰባት አመታት ሁሉም ቤተሰብ ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመርና ከአማራጭ ኤነርጂ ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠይቅም ተናግረዋል።

በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የኤነርጂ ኢንስቲቱዩት ዳሬክተር ዶክተር አስፋው ኃይለስላሴ በበኩላቸው  ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ የሀይል አማራጮች ጥናትና ምርምር እያሔደ ይገኛል ብለዋል።

በንፋስና ጸሀይ ብርሀን የሚሰራ የሀይል አማራጭ  ምርምር ማካሄድና ቴክኖሎጂዎችን የማፍለቅ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ገልጸው በክልሉ ሀገረሰላም፣አጽቢና እዳጋ ሓሙስ ደግሞ ከንፋስ ሀይል ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ጥናት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ዩኒቨርስቲው በቀጣይ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑንም አስረድተዋል።

በአውደ ጥናቱ ላይ ከአዲስ አበበና ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎች፣ከውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴርና ከክልሉ የተለያዩ ቢሮዎች የተወከሉ ባለሞያዎች ተሰታፊ ሆኖዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዳማ ቁጥር ሁለት የንፋስ ሀይልን ጨምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ለ1 ሺህ 409 የጤና ተቋማት የተተከሉ በጸሀይ ብርሀን የሚሰሩ መሳሪያዎችን የመግጠም ፕሮጀክት አማካሪ ሆኖ መስራቱን ከዩኒቨርሲቲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ