አርዕስተ ዜና

በትግራይ በተካሄደ የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ ጥንታዊ ከተማ ተገኘ

27 Dec 2017
789 times

ሽሬ እንዳስላሴ ታህሳስ 18/2010 በትግራይ ክልል በተካሄደ የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ ጥንታዊ ከተማ መገኘቱን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

ከተማው የተገኘው በክልሉ ከሽሬ እንዳስላሴ ከተማ በቅርብ ርቀት በሚገኘውና ‘‘ማይአድራሻ‘‘ በተባለ ስፍራ እንደሆነ ተገልጿል ።

በቢሮው የአርኪኦሎጂ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ግደይ ገብረእግዚአብሔር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት ከተማው ከክርሰቶስ ልደት በፊት 1ሺህ 250 ዓመት የነበረ ስለመሆኑ ታውቋል።

በካሊፎርንያ ዩኒቨርስቲ የአርኪዮሎጂ ባለሞያዎች ፣ በቅርስ ጥበቃ እንክብካቤና ጥናት ባለሥልጣንና በትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ትብብር ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በተከናወነ ቁፋሮና ምርምር  ከተማው መገኘቱን ተናግረዋል ።

የቁፋሮ ሥራው ቀደም ሲል በእንግለዝ አርኪኦሎጂስቶችና የቅርስ ተመራማሪዎች ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም በበጀት እጥረትና በሌሎች ምክንያቶች ተቋርጦ መቆየቱን አስታውሰዋል።

"በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ ሙሉ ወጪ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተካሄደ ቁፋሮ የተገኘው ከተማ ከ700 በላይ ጥንታዊ ቤቶች አሉት" ብለዋል።

እንደ ባለሞያው ገለፃ ጥንታዊ ቤቶቹ የተለያየ ቅርፅና ስፋት ያላቸውና ከድንጋይ የተሰሩ ናቸው።

የአርኪኦሎጂው ቁፋሮ አስተባባሪ ሚስ ዊሊክ ዎንድርች በበኩላቸው "የተገኘው ጥንታዊ ከተማ እንደ ንግስተ ሳባ ቤተ-መንግስት ቱሪስቶችን የመሳብ ኃይል ያለውና የጥንታዊ ሰዎችን አኗኗር የሚያሳይ ነው " ብለዋል ።

ከቤቶቹ ጋር ተያይዞ በአካባቢው ብረት ይቀልጥ እንደነበር የሚያረጋግጡና የእባብ ጭንቅላት ቅርፅ ያላቸው ጥንታዊ ቁሳቁሶች መገኘታቸውን አመልክተዋል።

በስፍራው የሚደረገውን ቁፋሮና ምርምር በስፋት ለማከናወን እቅድ መያዙን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በቁፋሮ የተገኙትን ለቱሪዝም አገልግሎት ለማዋል  ደረጃውን የጠበቀ ሙዝየም ለመገንባት እቅድ መያዙንም ጠቁመዋል ።

"በቁፋሮው የተገኙ ልዩ ልዩ ቀሳቁሶችንም ለጊዜው በዞኑ መስተዳድር ቅጥር ጊቢ አንድ ክፍል ውስጥ እንዲከማቹ ተደርጓል " ብለዋል ።

የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍሬህይወት ገብረ መድህን በበኩላቸው "በቁፋሮ የተገኙት ጥንታዊና ታሪካዊ ቤቶች በከተማው ነዋሪዎችና ተመራማሪዎች እየተጎበኙ ናቸው " ብለዋል ።

ከሽሬ እንደስላሴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አበራ ፀሃየ እንዳሉት በቁፋሮ የተገኙት ቤቶች  ጥንታዊ ታሪካችንን እንድናውቅ ከማድረግ ባለፈ ለከተማው እድገትና ብልፅግና የራሳቸው አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብለዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ