አርዕስተ ዜና

አየር መንገዱ አገልግሎቱን ቀልጣፋ የሚያደርግ የሞባይል አፕሊኬሽን ይፋ አደረገ Featured

07 Dec 2017
835 times

አዲስ አበባ ህዳር 28/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎቱን የሚያቀላጥፍ የሞባይል አፕሊኬሽን ይፋ አደረገ።

አዲሱ አሰራር አየር መንገዱ የሚሰጣቸውን የተለያዩ አገልግሎቶችን የያዘ ሲሆን ደንበኞች የበረራ ቀጠሮ ማስያዝና ሌሎች ጉዳዮችን በቀላሉ መከወን ያስችላቸዋል።

በአገልግሎቱ አማካኝነት ደንበኞች በረራቸውን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚያገኙም አየር መንገዱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። 

የሞባይል አፕሌኬሽኑን የሚጠቀሙ ደንበኞች ለበረራ ቀጠሮ ሲያሲዙ ከሚከፍሉት ገንዘብ የ10 በመቶ ቅናሽ ያገኛሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንደገለጹት የሞባይል አፕሊኬሽኑ አየር መንገዱ ካለው ስትራቴጂ ውስጥ በዋንኛነት የሚጠቀስ ነው።

በዚህም የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን በመጠቀምና አፍሪካዊ ጣዕም ያለው ኢትዮጵያዊ አገልግሎት በመስጠት የደንበኞችን የበረራ ጊዜ ምቹ ማድረግ እንደሚያስችለው ገልጸዋል።

አየር መንገዱ የደንበኞችን የበረራ ፍላጎት ለማሟላት ደንበኛ ተኮር የሆኑ የተለያዩ አገልግሎቶችን ተደራሽ እያደረገ መሆኑንም ገልጿል።

ተግባራዊ የሆነው የሞባይል አፕሊኬሽን አየር መንገዱ የደንበኞችን አገልግሎት ለማሻሻል እያከናወነ ላለው ስራ እንደ ማሳያ የሚወሰድ እንደሆነ ተነግሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የደንበኞችን አገልግሎት እንደሚያሻሽል የታመነበት አዲስ የአቪዬሽን ሕብረት እንዲቋቋም መወሰኑንና ለዛም የሚሆን አዲስ አደረጃጀት ማጽደቁ የሚታወስ ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ