አርዕስተ ዜና

ዘመናዊ የሰብል ምርት መሰብሰቢያ መሳሪያዎች እጥረት እንዳለባቸው የምስራቅ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ

05 Dec 2017
1050 times

ደብረማርቆስ ህዳር 26/2010 ዘመናዊ የእርሻና የምርት መሰብሰቢያ መሳሪያዎች እጥረት እንዳለባቸው የምስራቅ ጎጃም ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ።

አርሶ አደሮቹ በግብርና ባለሙያዎች የሚሰጠው ስልጠናና የግብዓት አቅርቦት የተሻለ ቢሆንም ዘመናዊ የእርሻና የምርት መሰብሰቢያ መሳሪያዎችን በመጠቀም በኩል እጥረት እንዳለ ነው የተናገሩት።

በዞኑ ጤፍና ስንዴ በብዛት የሚመረት ከመሆኑ በላይ የመልክዓ ምድሩ አቀማመጥ የተመቸ ቢሆንም ከስንዴ መውቂያ ኮምባይነር ውጭ ሌሎች መሳሪያዎች የሉም።

በዞኑ ጤፍ በብዛት በሚመረትበት ሸበል በረንታ ወረዳ ወይንዬ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ አብዩ አገዘ እንዳሉት ምርጥ ዘር በመጠቀምና ጤፍን በመስመር በመዝራት ካለፈው አመት  የተሻለ አዝመራ ቢይዙም የሚያጭዱትም ሆነ የሚወቁት በሰው ጉልበት መሆኑን ይገልጻሉ።

ይህም ምርት በወቅቱ እንዳይሰበስብና እንዲባክን ያደርጋል ብለዋል።

አርሶ አደሮቹ ለጤፍ የሚሆን የእርሻም ሆነ የመውቂያ መሳሪያ እንዳላገኙ ነው የገለፁት።

በአንፃሩ በስንዴ ምርት በሚታወቀው የደብረ ኤልያስ ወረዳ አርሶ አደሮች ጥቂት የሚባሉ የስንዴ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች ወይም ኮምባይነር ቢኖሩም በቂ እንዳልሆነና የእርሻ ትራክተር እንዳላገኙ ተናግረዋል።

በወረዳው የቀጋት ቀበሌ ነዋሪ የሆነው ወጣት አንማው አንዷለም ስንዴውን በኮምባይነር እንዳሳጨደ እና በሰው ጉልበት ከአንድ ሳምንት በላይ የሚፈጀውን በኮምባይነር በሃያ ደቂቃ እንደጨረሰ ይናገራል።

ወጣት አንማው ጊዜና ጉልበት ቢቆጥብለትም የኮምባይነር እጥረት በመኖሩ ለማሳጨድ ወረፋ እንዳለ እንዲሁም በትራክተር ማሳረስ ቢፈልግም ትራክተር እንዳላገኘ ገልጿል።

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አዝመራው አባተም የኮምባይነር መሰብሰቢያ ውጤታማ እንዳደረጋቸው ገልፀው የምርት ስብሰባው ሲያልቅ ወደ መስኖ ስራ ስለሚገቡ የእርሻ ትራክተር እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።

መንግስት እንደ ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር ሁሉ ትራክተርም ቢያቀርብልን የበለጠ ውጤታማ እንሆናለን በማለት ነው ፍላጎታቸውን ገለፁት።

የሸበል በረንታ ወረዳ የሰብል ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አንዳርጋቸው አለማየሁ አርሶ አደሩን በማሰልጠንና ተፋሰሱን በማልማት ምርትን መጨመር ቢቻልም ግብርናውን በቴክኖሎጂ ከማገዝ አኳያ ክፍተት አለ ብለዋል።

የወረዳው አርሶ አደር ጤፍንና ማዳበሪያን አንድ ላይ መዝራት የሚያስችል መሳሪያ የመጠቀም ፍላጎት ቢኖረውም የአቅርቦት ችግር እንዳለ ገልፀዋል።

የደብረ ኤልያስ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳዘዝ ጎዴ በበኩላቸው በወረዳው 30 ኮምባይነሮች ቢኖሩም 28ቱ የመጡት ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ አካባቢ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

ከአቅርቦት እጥረቱ ባሻገር አብዛኛዎቹ መሳሪያዎች ራቅ ካለ ቦታ መምጣታቸው አርሶ አደሩ ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳስከተለ ገልፀዋል።

አርሶ አደሩ በትራክተር የማረስ ፍላጎት ቢኖረውም ወረዳው ላይ ትራክተር የለም ብለዋል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን አቢታ አርሶ አደሮች በቅድመ ምርትም ሆነ በድህረ ምርት መሳሪያዎችን እንዲጠቀሙ ለማስቻል እየተሰራ ነው ብለዋል።

ባለፉት ሁለት አመታት ዞኑ በግል አቅራቢዎችና በመንግስት በኩል መሳሪያዎችን ሲያቀርብ እንደነበር ጠቁመዋል።

በዚህ አመትም በዞኑ ሶስት ስንዴ አምራች ወረዳዎች 41 ኮምባይነሮችን እንዳስገቡ ገልፀዋል።

አቶ ፋንታሁን የአርሶ አደሩን ፍላጎት ለማሟላት እንደዘገዩ ገልፀው በዚህ አመት ሌሎች ኮምባይነሮችና ትራክተሮችን ለመግዛት ሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ