አርዕስተ ዜና

ስድስት ከመቶ የካንሰር መንስኤ ከመጠን በላይ ውፍረትና የስኳር በሽታ ናቸው -ጥናት

30 Nov 2017
1372 times

ህዳር 21/2010 “በአለም አቀፍ ደረጃ ስድስት ከመቶ ለካንሰር መንስኤ የሚሆኑት ከልክ ያለፈ ውፍረትና ስኳር በሽታ አመጋገባችን ምን መሆን እንደሚገባው እንድናጤን የሚያስገድድ ነው “ይላል ዩ ፒ አይ ያወጣው አዲስ የጥናት  መረጃ፡፡ 

“ከልክ ያለፈ ውፍረትና የስኳር በሽታ በግለሰብ፣በማህበረሰብ፣በጤና አጠባበቅና ፖሊሲ ጣልቃ ገብነት ልንከላከላቸው የምንችል የካንሰር መንስኤዎች ናቸው” ያሉት ዶክተር ግርሃም ኮልዲቲዝ ሴንት ሊዊስ ከሚገኘው የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት ነው፡፡ 

ለዚህም “ሰዎች በህይወት ዘመናቸው ሁሉ የተስተካከለ ክብደት እንዲኖራቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል”ብለዋል ዶክተር ኮልዲትዝ፡፡

የስኳር በሽታና ከልክ ያለፈ ውፍረት በሚያመጡት የስነህይወት ለውጥ  የደም ውስጥ የሥኳር መጠን ይጨምራል፣የከፋ የሰውነት መቆጣትና  የጾታ ሆርሞኖች መዛባት ያስከትላል፤ ይህም በጊዜ ሂደት ወደ ካንሰር ሊያመራ ይችላል ያሉት ደግሞ የእንግሊዝ አጥኚዎች ናቸው ፡፡

የጥናት ውጤቱ ላይ ለመድረስ ከ175 ሃገራት የተወጣጡ የጤና መረጃዎች የተተነተኑ ሲሆን በደረሱበት መደምደሚያም እኤአ በ2012 ያልተመጣጠነ የሰውነት ክብደትና የስኳር በሽታ 5.6 ከመቶ ለካንሰር ድርሻ እንደነበራቸው ታውቋል፡፡    

ከልክ ያለፈ ውፍረት ለካንሰር 4 ከመቶ ድርሻ ሲኖረው የስኳር በሽታ ደግሞ 2 ከመቶ እንደሆነ አጥኚዎቹ ገልፀዋል ፡፡

በተለይም ሁለተኛው አይነት የስኳር በሽታ ከእንቅስቃሴ መወሰን የሚከሰትና ከልክ ላለፈ ክብደት የሚዳርግ እንደሆነ ዘገባው ጠቁሟል ፡፡

ከልክ ባለፈ ውፍረትና ስኳር በሽታ ምክንያት ካንሰር የሚከሰትባቸው አብዛኛውን የምእራብ ሃገራትና፣የምስራቅና የደቡብ ምስራቅ የኤሺያ ሃገራት እንደሆኑም  ጥናቱ ጠቁሟል ፡፡ 

በአለም አቀፍ ደረጃ 422 ሚሊየን ጎልማሶች የስኳር በሽታ እንዳለባቸው ሲገመት 2 ቢሊየን ሰዎችም ከልክ በላይ ውፍረት አለባቸው ፡፡ 

ለካንሰር አጋላጭ ሁኔታዎች እየጨመሩ በመምጣታቸው መንስኤዎቹን መከላከልና መለየት ላይ ማተኮር እንደሚገባ የገለፁት ደግሞ የጥናቱ መሪ ዶክተር ጆናታን ፒያርሰን ስቱታርድ ከለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ ናቸው፡፡

ዶክተር ኮልድቲዝ በሰጡት ማጠቃለያ አጋላጭ ሁኔታዎችን መከላከል ካልቻልን  በሰውነት ክብደት አለመመጣጠንና በስኳር ህመም የሚመጣው ካንሰር አለም አቀፍ ጫና ማሳደሩን እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ