አርዕስተ ዜና

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሰራው የእምቦጨ አረም ማስወገጃ ማሽን በጣና ሐይቅ ላይ የሙከራ ስራ ጀመረ Featured

28 Nov 2017
1352 times

ጎንደር ህዳር 19/2010 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ የሰራው ተንሳፋፊ የአረም መሰብሰቢያ ማሽን በጣና ሐይቅ ላይ የመጀመሪያውን የሙከራ ስራ ጀመረ፡፡

በጎርጎራ ወደብ አካባቢ ዛሬ የሙከራ ስራ እንዲጀምር የተደረገው ማሽን በሰዓት 50 ኩንታል የእምቦጭ አረም ሰብስቦና ፈጭቶ ከሐይቁ የማስወገድ አቅም አለው ተብሏል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ኘሬዚዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ ''ወደ ሙከራ ስራ የገባው የእምቦጭ አረም መሰብሰቢያና ማስወገጃ ማሽን ላለፈው አንድ ዓመት በዩኒቨርሲቲው የኢንጅነሪግ ክፍልና አጋር አካላት ከፍተኛ ጥረት እውን የተደረገ ነው''ብለዋል፡፡

''ዩኒቨርሲቲው ለቴክኖሎጂ ፈጠራ በቀጣይም ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል'' ያሉት ኘሬዚዳንቱ ማሽኑን በአጭር ጊዜ ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስገባት ርብርብ እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መስፍን ማሽኑን በማጓጓዝ በሐይቁ ላይ ከማንሳፈፍ ጀምሮ የእምቦጭ አረም የመሰብሰብ አቅሙን የመፈተሽ ስራ ሲከናወን መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ይኸው ማሽን በሰዓት 50 ኩንታል የእምቦጭ አረም ሰብስቦና ፈጭቶ ከሐይቁ ላይ የማስወገድ አቅም እንዳለው ገልፀዋል፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በጣና ሐይቅ ህልውና ላይ ስጋት የደቀነው የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ተጨማሪ ሁለት ማሽኖችን በተከታታይ ሰርቶ አገልግሎት ላይ ለማዋል ቀጣይ እቅድ እንዳለው ታውቋል፡፡

የአማራ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጅ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ኮሚሽነር ዶክተር ሰብስበው  አጥቃው በበኩላቸው ኮሚሽኑ ይህን መሰል አገር በቀል የፈጠራ ስራ በመደገፍ ለቴክኖሎጂ የእውቀት ሽግግር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

''የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያከናወነው የፈጠራ ቴክኖሎጂ ለሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች ሞዴልና ፈር ቀዳጅ ነው'' ያሉት ደግሞ ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶክተር አልማዝ አፈራ ናቸው፡፡

በማሽኑ የሙከራ ማስጀመር ስነስርዓት ላይ የጎንደር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የባህር ዳር፣ የወሎና የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ ተመራማሪዎችና ባለሙያዎች ተካፋይ ሆነዋል፡፡

በሰሜን ጎንደር የሚገኙትን የጎንደር ዙሪያ ፣ የደንቢያና ፣ የጣቁሳ ወረዳዎችን የሚያዋስነው የጣና ሐይቅ በጥናት በተለየው መሠረት 6 ሺህ ሄክታር የሐይቁ አካል በእምቦጭ አረም ተወሯል፡፡

አረሙን በህዝብ ንቅናቄ የማስወገድ ዘመቻ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ