አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

በሞሪንጋ ተክል ላይ የሚካሄደው ምርምር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ቀዳማዊ እምቤት ሮማን ተስፋዬ አሳሰቡ

14 Nov 2017
1197 times

ሀዋሳ ህዳር 5/2010 የሞሪንጋ ተክል ከምግብነት ባለፈ የተለያዩ ጠቀሜታዎችን መስጠት እንዲችል በምርምር መስክ እየተከናወነ ያለው ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ቀዳማዊ እምቤት ሮማን ተስፋዬ አሳሰቡ፡፡

"የሞሪንጋን ዕምቅ አቅም ለላቀ ጥቅም ማዋል" በሚል መሪ ቃል በሞሪንጋ ተክል ላይ የሚመክር መድረክ ዛሬ በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሂዷል፡፡

ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ በተወካያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ሞሪንጋ (ሀለኮ) በሚበቅልባቸው አካባቢዎች ሕብረተሰቡ ለምግብነት እየተጠቀመበትና በንጥረ ምግብ ይዘቱ የበለጸገ እንደመሆኑ መጠን ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ አልተሰራም፡፡

ወይዘሮ ሮማን እንዳሉት በሕብረተሰቡ ላይ በቂ ግንዛቤ ባለመፈጠሩና ከአጠቃቀም በሚስተዋሉ ውስንነቶች የተነሳ ከተክሉ ማግኘት የሚቻለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ማግኘት እየተቻለ አይደለም፡፡

"በሞሪንጋ ተክል ላይ የተለያዩ ችግር ፈቺ ምርምሮች እየተካሄዱ ቢሆንም የዘርፉ ተመራማሪዎች ተክሉ ሊሰጠው ከሚችለው ጠቀሜታ አንጻር አሁንም ገና ያልተዳሰሱ በርካታ ጥናትና ምርምር የሚጠይቁ ጉዳዮች እንዳሉ በመረዳት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል" ብለዋል፡፡

የሞሪንጋ ተክል ከምግብነት ባለፈ በተለያዩ መንገዶች ተቀነባብሮ ለመድኃኒትነት፣ ለመዋቢያ ምርቶች ግብዓትነት፣ ለእንስሳት መኖነትና ለአፈር ለምነት ጥቅም ላይ ለማዋል ከሌሎች ሀገሮች ምርጥ ተሞክሮ መቀመርና በጥናት መደገፍ እንደሚገባም ቀዳማዊት እመቤቷ አሳስበዋል፡፡

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ሚንስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሳ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ሞሪንጋ (ሀለኮ) እየተባለ የሚጠራው ተክል ሀገራዊ ፋይዳ እንዲኖረው ለማድረግ በመስኩ በርካታ ምርምሮች እየተካሄዱ ናቸው፡፡

በዋናነት በደቡብ ክልል በጋሞጎፋ ሰገን ሕዝቦችና ደቡብ ኦሞ ዞኖች በስፋት የሚበቅለውን ይህን ተክል ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለተለያዩ አገልግሎቶች እንዲውል ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አዲስ ግኝቶች እየታዩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር በመስኩ ለሚከናወኑ ምርምሮች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ባለው የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ሳምንት ውስጥ ተክሉ ትኩረት ተሰጥቶው ውይይት እንዲደረግበት ተወስኖ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደሴ ዳልኬ በተወካያቸው በኩል እንዳሉት በክልሉ መንግስት የሥራ ዕድል ፈጠራ መርሀ ግብር በሞሪንጋ ማቀነባበር ዘርፍ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል፡፡

እንደርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ ሞሪንጋ በክልሉ የምግብ ዋስትና ላይ ጉልህ ድርሻ እንዳለውና ይህንን በሳይንሳዊ ዘዴ ደግፎ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ ጅምር ሥራዎች አሉ፡፡

በተክሉ ላይ የሚደረጉ ምርምሮችን ለማገዝ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡

የሞሪንጋ ተክል በአካባቢው አጠራር ሀለኮ እና ሽፈራው በመባል ይታወቃል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ