አርዕስተ ዜና

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተደራሽና ተወዳዳሪ ተቋም ለመሆን የጀመረውን ጥረት መቀጠል አለበት- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2010 የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ ተወዳዳሪና ተደራሽ የዜና ምንጭ ለመሆን የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ።

የምክር ቤቱ የባህል፣ ቱሪዝምና መገናኛ ብዙሃን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  ዛሬ በኤጀንሲው የመስክ ምልከታ አድርጓል።

በምልከታውም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንደገለፁት፤ ተቋሙ በጥራትና ለውጥ ቡድን እንቅስቃሴ፣ በእቅድ አዘገጃጃትና ትግበራ፤ ተደራሽነቱን ለማስፋት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ የሚበረታታ ነው። 

በተለይ ባለፉት ጊዜያት በምክር ቤቱ የተሰጡትን ግብረ መልሶች ተቀብሎ ተግባራዊ በማድረግ፤ በኦዲተር የተሰጡ መልካም አስተያየቶች ይበልጥ በማሳደግና የተመደበለትን በጀት በአግባቡ በመጠቀምም የተሻለ ስራ ማከናወኑን ገልጻዋል።

በተጨማሪም ትኩረት በሚሹ አካባቢዎች በሁመራ፣ በሰቆጣና በመተማ አካባቢዎች ቅርንጫፎችን በመክፈትና በሁሉም የአገሪቷ ክልሎች ተደራሽ ለመሆን እያከናወነ ያለውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ወይዘሮ ሞሚና ማሀመድና አቶ ጠይብ አባፎጊ እንዳሉት ተቋሙ ወቅታዊ ዜናዎችን  ለህብረተሰቡ ለማድረስ የጀመራቸው የኦን ላይን ቴሌቪዥንና ፌስ ቡክን ጨምሮ በተለያዩ ማሕበራዊ ድረ-ገጾች መረጃን የማድረስ ስራዎቹን በጥንካሬ ማየታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሬዲዮና የቴሌቪዥን ስቱዲዮዎችን ያካተተ አዲስ የሚዲያ ኮምፕሌክስ በማስገንባት የተቋሙን ተደራሽነት ለማስፋት እየተደረገ ያለውን ጥረት በመልካም ጎኑ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ቋሚ ኮሚቴው በቀጣይም ከሰራተኛ ጥቅማ ጥቅምና የደሞዝ ጥያቄ ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎች ግልጽና አሳታፊ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ሃሳቦችን ማስተናገድ እንዳለበት አሳስበዋል።

የሰራተኛው የውስጥ ውድድሮችን ህጉ በሚፈቅደው መሰረት በማካሄድ፣ ግልጸኝነትን ማስፈንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከውጪና ከውስጥ በመለየት ፈጣን መፍትሄ መስጠት አለበትም ብለዋል።

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ሙለታ በበኩላቸው ከሰራተኛው ለሚነሱ የደመወዝና ሌሎች ጥያቄዎች ተቋሙ እያካሄደ ያለው የመዋቅር ጥናት ምላሽ ይሰጣል ብለዋል።

በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙ የሚያጋጥሙትን ችግሮች በቅርበት ለመፍታት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

Last modified on Thursday, 05 April 2018 02:51
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን