አርዕስተ ዜና

በኢትዮጵያ ሁኔታዎችን በመገምገም ቀድመው የሚያሳውቁ ጠንካራ መገናኛ ብዙሐንን መፍጠር እንደሚገባ ምሁራን ገለጹ

07 Nov 2017
1475 times

አዲስ አበባ ጥቅምት28/2010 በኢትዮጵያ ሁኔታዎችን በመገምገም መረጃዎችን ቀድመው የሚያሳውቁ ጠንካራ መገናኛ ብዙሐንን መፍጠር እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

 በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ ያሉ የመገናኛ ብዙሃና ጠንካራ አቅም ባለመፍጠራቸው ሕዝቡ ትኩረቱን ወደ ማሕበራዊ ሚዲያዊ እንዲያደርግ መገደዱንም ነው የሚናገሩት።

 አስተያየታቸውን የሰጡት የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት ጠንካራ የመገናኛ ብዙሃን ከተፈጠሩ በግጭቶችና በሌሎች ጉዳዩች ዙሪያ ከተለያዩ አካባቢዎች ቅድመ መረጃዎችን በመሰብሰብ ሕብረተሰቡን ካላስፈላጊ ችግሮች የመጠበቅ አቅም እንዲያገኙ ያደርጋል።

 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሸን ትምህርት ክፍል ለረጅም ዓመታት በመምህርነት ያገለገሉት ዶክተር ገብረመድሕን ስምኦን እንዳሉት ''በአገሪቱ ያሉት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ባለሙያዎች የሕዝቡን ስሜትና ፍላጎት ይዞ በመንቀሳቀስ ረገድ ክፍተቶች አሉባቸው።''

 ''አንዳንድ ቦታዎች ግጭቶች ሊፈጠሩ ሲሉ ምልክቶች ይታያሉ በመሆኑም መገናኛ ብዙሃኑ ያሏቸውን  መዋቅሮች ተጠቅመው ግጭቶችና ሌሎች ምልክቶችን ቀድመው ማወቅ እንዲችሉ አቅማቸውን ማጠናከር ይገባል'' ነው ያሉት።

 መረጃዎቹን ቀድመው ማግኝታቸውም ሕዝብና መንግስት በሕብረተሰቡ መካከል ያሉትን ችግሮች ቀድመው እንዲፈቱና ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከማስቻሉም ባለፈ የመንግስትን ፖሊሲ እስከማስቀየር እንደሚያደርሳቸው ነው ያመለከቱት።

 በተጨማሪም መገናኛ ብዙሃን ሕዝብን በማንቃትና ትክክለኛ የሆነ መረጃ በማቅረብ በሁከቶችና ግርግር ምክንያት ሊመጡ የሚችሉትን የሰው ህይወትና የሃብት ውድመት የመታደግ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አብራርተዋል።

 ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገሮች በአብዛኛው ለግጭቶች መባባስ ምክንያት ሕዝብ ትክክለኛና ተአማኒነት ያለው መረጃ አለማግኘቱ መሆኑን አመልክተው፤ እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላትም በተለይ የሕዝብ መገናኛ ብዙሃንን አቅም ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸል።

 በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ጠንካራ አቅም ሊፈጥሩ ባለመቻላቸውና ትክክለኛ መረጃን ቀድመው ለሕዝቡ ባለማድረሳቸው ሕዝቡ ትኩረቱን ወደ ማሕበራዊ ሚዲያዊ እንዲያደርግ እድል መክፈቱን ተናግረዋል።

 ''እነዚሁ የማሕበራዊ ሚዲያዎች ገነው የሚወጡትና ትክክለኛም ሆነ የሐሰት መረጃዎችን በፍጥነት ለማራገብ እድሉን የሚያገኙት ዋናው ወይም ሜንስትሪም ሚዲያው መረጃዎችን ደብቋል ብለው ሲያስቡ እንደሆነ'' ነው የሚገልጹት።

 በመሆኑም መገናኛ ብዙሃን ጠንካራ አቋም እንዲኖራቸውና የሕዝቡን የመረጃ ፍላጎት በማርካት ረገድ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባም ነው ያመላከቱት።

 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሸን መምህር ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ እንደሚሉት፤ በአገሪቱቷ በተለይ ግጭቶች በሚነሱበት ወቅት የመገናኛ ብዙሃን ማሕበራዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይገባቸዋል።

 ከሕዝቡ ቀድመው ትክክለኛ መረጃዎችን በማደራጀትና ግጭቱ ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጣ ማድረግ እንዲችሉም ጉዳዩችን የመተንተን ፣ ባለሙያዎችንና የተለያየ አመለካከት ያላቸውን አካላት የማወያየት ስራ ላይ በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

 የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተለይ ግጭቶችን በሚዘግቡበት ወቅት ሕዝብን ከሕዝብ የማያጋጩ ፤ወደ አንድ ወገን ያላዘነበሉና ሰላምን የሚያስገኙ መረጃዎችን ማቅረብ አለባቸው ብለዋል።

 ''እንደ ባለሙያም ግጭቱ በተነሳበት አካባቢ ያሉትን ወገኖች በማወያየትና ሐሳባቸውን በግልጽ እንዲያስቀምጡ መድረኮችን ካመቻቹ በኋላም አንድ የሚያደርጓቸውን ሐሳቦች በማጉላት መተማመንን ማምጣት ይችላሉ'' ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ።

 የመንግስትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ባለሙያዎች የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባርና መርሕን ተከትለው እንዲሰሩና ተጽእኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ አቅማቸውን ማጠናከር እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

 በመጨረሻም ግጭቶቹ ከተከሰቱም በኋላ በተቋማቱ ጥልቅ የሆነና አርቀው የሚያስቡ አርታእያን መኖር የሚለቀቁትን መረጃዎች መጥፎም ጥሩም ተጽእኖ በጥልቀት አስበው በኃላፊነት እንዲሰሩ ያስችላል ብለዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ