አርዕስተ ዜና

ትልማ ለሚያስገነባቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላት የ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተገኘ

05 Nov 2017
1393 times

መቀሌ ጥቅምት 26/2010 የትግራይ ልማት ማህበር (ትልማ) በክልሉ ለሚያስገነባቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላት ድጋፍ ለማግኘት ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር የ6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተገኘ።

ማህበሩ ትናንት በመቀሌ ከተማ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብሩን ያዘጋጀው በክልሉ 37 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚያስገነባቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላት ነው።   

የልማት ማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ታደለ ሀጎስ በእዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ማህበሩ ማዕከላቱን ለማስገንባት ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ያለው ከትምህርት ጥራት ጋር በተያያዘ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚታየውን ችግር ለማቃለል ነው።

ዶክተር ታደለ እንዳሉት፣ ማህበሩ ትላንት በመቀሌ ከተማ ባዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግብር ላይ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል ተገብቶለታል ።

የሚገነቡት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላት ባለ አንድ ፎቅ ሕንጻ ሲሆኑ ለሳይንስ ቤተሙከራ፣ ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ለዲጅታል ቤተንባብና ለሌሎች አገልግሎት መስጫ የሚውሉ ክፍሎች እንደሚኖራቸው ተመልክቷል።

ማህበሩ እስካሁን የአምስት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማዕከላት ግንባታ ሥራን ያጠናቀቀ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ በመጀመሪያ የግንባታ ምዕራፍና በዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ ዶክተር ታደለ ገልጸዋል፡፡

ትናንት በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሀ ግበር ላይ 120 ሺህ ብር ለመለገስ ቃል ከገቡ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ሀጂ መሀመድ ዓብደላ አንዱ ናቸው፡፡

"ልማት ማለት የሰውን አዕምሮ ማልማት እንጂ ብር መሰብሰብ ብቻ አይደለም" ሲሉም ሀጂ መሀመድ ተናግረዋል።

ለማዕከላቱ ግንባታ ድጋፍ የሚውል አንድ ሚሊዮን ብር ለመስጠት ቃል የገቡት ደግሞ አቶ ይርዳው መኮንን የተባሉ ባለሀብት ናቸው፡፡                                                                                                         

ባለሀብቱ ቃል ከገቡት ገንዘብ በተጨማሪ በየዓመቱ በአባልነት ይከፍሉት የነበረው 25 ሺህ ብር ወደ አንድ መቶ ሺህ ብር ከፍ እንዲል ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

"በሳይንስና ቴክኖሎጂ የዳበረ ማህበረሰብ ከተገነባ በአገራችን  የተሻለ ልማት እንደሚኖር በመተማመን ለልማት ማህበሩ ድጋፍ አድርጊያለሁ" ብለዋል፡፡

 የትግራይ ልማት ማህበር "8160" ላይ አጭር የጽሁፍ መልዕክት በመላክ ገቢ ለማሰባሰብ ዕቅድ ይዞ እንቅስቃሴ መጀመሩም በገቢ ማሰባሰቢያ መድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡

 የትግራይ ልማት ማህበር ባለፉት 26 ዓመታት የክልሉ ምንግስት ባልደረሰባቸው አካባቢዎች 691 አንድኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በማስገነባት ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡

 ከእዚህ በተጨማሪ ሁለት ሆስፒታሎች፣ አምስት ጤና ጣቢያዎችና 74 ኪሊኒኮች ማህበሩ ካስገነባቸው ማህበራዊ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ