አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የዕፅዋት አዳቃዮችን የባለቤትነት መብት የሚያሰጥ አዲስ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

04 Nov 2017
1478 times

አዲስ አበባ  ጥቅምት 25/2010 ዕፅዋትን ለሚያዳቅሉ አካላት የባለቤትነት መብት የሚያሰጥ አዲስ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ።

 የተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የዕጸዋት ምሁራን፣ከመንግስትና ከግል ተቋማት የመጡ ባለድርሻ አካላት የዕፅዋት አዳቃይ ረቂቅ አዋጅ ላይ ትናንት ተወያይተዋል።

 የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ተስፋየ መንግስቴ ነባሩን  የአዋጅ ቁጥር 481/1998 ተግባራዊ የሚያደርጉ ተቋማት በሚገባ አለመደራጀታቸውና አዋጁ ከዓለም አቀፍ አሰራሮች ጋር የማይሄዱ ጉዳዮችን በመያዙ አስካሁን ሳይፈጸም መቆየቱን ለምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል።

ነባሩ አዋጅ የፈጻሚው አካል ተግባርና ሃላፊነት በአዋጁ በግልጽ ባለመቀመጡ ይህንን በአዲስ አዋጅ ማካተት በማስፈለጉና የዕፅዋት አዳቃዮች መብት የቆይታ ጊዜ አሰላል ከዓለም አቀፍ ልምድ ጋር ተቃኝቶ እንዲሰላ በማስፈለጉ ስለ አዲሱ አዋጅ አስፈላጊነት ተናግረዋል።

 በአዲሱ አዋጅ የዕፅዋት አዳቃዩ የባለቤትነት መብት ጥበቃ ዘመን መቆጠር የሚጀምረው የዕፅዋት አዳቃይ መብት ከተሰጠበት  ዕለት አንስቶ ሲሆን፣ ዓመታዊ ሰብሎችን በተመለከተ ለ20 አመታት ፣ዛፎች፣የወይን ተክሎች ወይም ሌሎች ቋሚ ተክሎችን በተመለከተ ለ25 አመታት ይሆናል።

 አዲሱ የዕፅዋት አዳቃይ አዋጅ ኢትዮጵያዊም ይሁን የውጭ ዜጋ ፣ ነዋሪነቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆንም ባይሆንም ዝርያው ኢትዮጵያ ውስጥ ይሁን ውጭ ሀገር የተዳቀለ አዲስ የዕፅዋት ዝርያ ከሆነ መብት እንዲሰጠው ይፈቅዳል።

 እንደ አዲስ እየተረቀቀ ባለው የዕፅዋት አዳቃይ መብት አዳቃዩ የግልም ይሁን የመንግስት ተቋም የዕፅዋት አዳቃይ መብቱ በድርጅቱ ስም እንደሚሰጠው የሚፈቅድ ሲሆን ነባሩ አዋጅ የመብት አሰጣጥ ሂደቱ በግልጽ የተቀመጠ አልነበረም።

 አዋጁ በተጨማሪ ያዳቀሉትን ዕፅዋት መሸጥ ወይም ሌሎች ሰዎች እንዲሸጡ፣ የማባዛትና ሌሎች ሰዎች እንዲያባዙ ፈቃድ መስጠት ያስችላል ።

 ከዚህ ባለፈ አዳቃዮች እንዲበረታቱና የተሻላ ቴክኖሎጂ እንዲያፈለቁ ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል።

 የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ መሰል አዲሱ የዕፅዋት ማዳቀል አዋጅ ተፈጻሚ እንዲሆን ቋሚ ኮሚቴው በትኩረት እንደሚከታተል ጠቅሰው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት እንደሚመራ ገልጸዋል።

 በኢትዮጵያ ከ 1 ሺህ 280 በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች እንዳሉ ከኢትዮጵያ ብዝሐ ሕይወት ኢንስቲትዩት መረጃዎች ያሳያሉ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ