አርዕስተ ዜና

የሰሜንና ሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ ተፋሰሶች እርጥበት እየቀነሰ እንደሚሄድ ገለጸ

05 Oct 2017
1973 times

አዲስ አበባ መስከረም 25/2010 በመጪዎቹ አምስት ቀናት በአብዛኛው ሰሜንና ሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ ተፋሰሶች ላይ እርጥበቱ እየቀነሰ እንደሚሄድ ብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ ገለጸ።

በሌላ በኩል የተራዘመ የክረምት ወቅት ዝናብ ያላቸው የምዕራብ አጋማሽና ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆነው የደቡብና ደቡብ ምስራቅ ተፋሰሶች የተሻለ እርጥበት የሚስተዋልበት ወር መሆኑን አስረድቷል።

ኤጀንሲው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ በአብዛኛው ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ጊቤ፣ገናሌ ዳዋና ስምጥ ሸለቆ፣የአባይ ደቡባዊና ምዕራባዊ አጋማሽ፣የታችኛው ተከዜ ከመደበኛ በላይ  የሆነ ዝናብ ያገኛሉ።

በተመሳሳይ የታችኛውና የመካከለኛው አዋሽ ፣ የላይኛውና የመካከለኛው ዋቢ ሸበሌ  እንዲሁም የኦጋዴን ተፋሰሶች መደበኛና በጥቂት ቦታዎች ከመደበኛ በላይ የሆነ ዝናብ ያገኛሉ ብሏል ኤጀንሲው።

ይህ ሁኔታ  በተለይ በደቡባዊ  አጋማሽ በሚገኙ በታችኛው ተፋሰሶች ላይ  ከላይ በሚመጣው የክረምት ዝናብ የወንዝ ፍሰትና የወቅቱ ዝናብ ጋር ተዳምሮ የጎርፍ ስጋት ሊያስከትል ስለሚችል ቅድመ ጥንቃቄ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁሟል።

ኤጀንሲው አያይዞ በምዕራብና በደቡብ አጋማሽ  የአገሪቱ ክፍሎች የተሻለ ገጽታ እንደሚኖራቸውና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክቷል።

ይህም ሁኔታ ወቅታዊ ዝናብ ማግኘት በሚጀምሩ በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች የማሳ ዝግጅት ለማድረግና ዘር ለመዝራት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስገንዝቧል።

ነገር ግን አልፎ አልፎ  ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል በመጠቆም በተለይም የደረሱ ሰብሎች እንዳይበላሹ  አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ኤጀንሲው አሳስቧል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ