አርዕስተ ዜና

ቢሮው ለተማራማሪ ወጣቶችና የጤና ባለሙያዎች ድጋፍና እውቅና መስጠቱን አስታወቀ

መጋቢት 23/2010 የትግራይ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ለተማራማሪ ወጣቶችና የጤና ባለሙያዎች የስልጠና ድጋፍና እውቅና መስጠቱን አስታወቀ።

ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለሃገር እድገትና ልማት መፋጠን ያለውን ፋይዳ አስመልክቶ ቢሮው ለወረዳ ምክር ቤት አባላት፣ አፈ ጉባኤዎችና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ያዘጋጀው የአቅም ግንባታ ስልጠና በአክሱም ከተማ ተካሂዷል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር አብረሃ ኪሮስ በስልጠናው መድረክ እንዳሉት፣መስሪያ ቤታቸው በተያዘው የበጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 280 ለሚሆኑ ተማራማሪ ወጣቶች የተለያዩ ሙያዊ ድጋፍና እውቅና ሰጥቷል።

በክልሉ በሚገኙ 32 ሆስፒታሎች ውስጥ ለሚሰሩ የህክምና ባለሙያዎችም ከጨረር አደጋ ራሳቸውን መከላከል እንዲችሉ የአጠቃቀም ትምህርትና ስልጠና መስጠቱን ተናግሯል።

በክልሉ የሚገኙ 28 ኮሌጆችን ጨምሮ ለተለያዩ ተቋማት አገልግሎት ሊውሉ የሚችሉና በሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃዎች ላይ ትኩረት ያደረጉ አራት ሺህ ያህል መረጃዎችን ማሰራጨታቸውንም ጠቅሰዋል።

የከተማና የገጠር ልማት  ለማፋጠን የሚያግዙ ስድስት ዓይነት የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራዊ ተደርጓል ዶክተር አብረሃ እንደገለጹት፡፡

በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣን ልማት ለማረጋገጥ በየደረጃው የሚገኙ የምክር ቤት አበላት በህዝብና መንግስት የተጣለባቸው ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የዓድዋ ከተማ ምክር ቤት አባል መምህር አስመላሽ አሳየሀኝ በበኩላቸው በከተማው የሚገኙ የሙያና ቴክኒክ ማሰልጠኛ ማዕከላት የሳይንስና ምርምር ስፍራ እንዲሆኑ የምክርቤት አባላት ክትትልና ድጋፍ እየሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የታህታይ ማይጨው ወረዳ ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ መኮንን  ወልደስምኦን" በሳይንሳዊ መንገድ መስራት ፈጣን ልማትና እድገት ማረጋገጥ እንደሚቻል አመላካች የሆኑ የፈጠራ ስራዎችን ጀምረናል" ብለዋል።

ወጣቶችና ምሁራን የሀገር እድገትና ብልፅግና ለማፋጠን የሚያስችሉ ምርምሮችን እውን በማድረግ ኃላፊነታቸው ሊወጡ እንደሚገባ ያመለከቱት የምክር ቤት አባላቱ  ይህንን በመደገፍም የድርኛቸውን እንደሚወጡ ተናግረል፡፡

በዓድዋ ከተማ ምክር ቤት የሴቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ መምህርት ያለም ገብረስላሰ እንዳሉት ስልጠናው እያንዳንዱ ስራ በሳይንሳዊ መንገድ እንዲታሰብና በተግባርም እንዲተረጎም የሚያችል ግንዛቤ ያስጨበጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በተካሄደው ስልጠና ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል የኮሪያ ተሞክሮ በኢትዮጵያ፣ የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በልማት ያለውን ፋይዳ የሚሉት  ይገኙበታል።

በስልጠናው ከ14 የክልሉ ወረዳዎች የተውጣጡ ከ180 በላይ የወረዳ ምክር ቤት አባላት፣ አፈ ጉባኤዎችና የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ተሳትፈዋል፡፡

 

Rate this item
(1 Vote)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን