አርዕስተ ዜና

70 የመንግስት ሆስፒታሎች ዘመናዊ የህክምና መረጃ አያያዝ ቴክኖሎጂ መጠቀም ይጀምራሉ

08 Sep 2017
2778 times

አዲስ አበባ ጳጉሜ 3/2009 በተያዘው በጀት ዓመት 70 የመንግስት ሆስፒታሎች ዘመናዊ የህክምና መረጃ አያያዝ ቴክኖሎጂ ወይም የኤሌክትሮ ሜዲካል ሪከርዲንግ ሲስተም በመጠቀም ህክምና መስጠት እንደሚጀምሩ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለፀ።

ቴክኖሎጂው የአንድን የጤና ተቋም ሁሉንም ክፍሎች በኔትወርክ በማገናኘት ከካርድ ክፍል ጀምሮ መርማሪ ሀኪሞች፣ የላቦራቶሪ ባለሙያዎች፣ መድሃኒት ቤትና የተለያዩ የምርመራ ክፍሎች በአንድ መረጃ እንዲጠቀሙ የሚያስችል ነው።

በሚኒስቴሩ የጤና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተር አቶ ኢዮብ ከበደ ለኢዜአ እንደተናገሩት በአምስት ዓመቱ የጤና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሰረት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም የጤና ተቋማት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሰራ ነው።

የህክምና ታሪኮችን መዝግቦ ስለሚይዝ የታካሚዎችን መጉላላት ይቀንሳል፣ የጤና ተቋማትን አሰራርም ያቀላጥፋል የተባለውን ቴክኖሎጂ ወደ አገልግሎት ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው የገለፁት።

የጤና ተቋማት በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ህመሞችና በብዛት የሚፈለጉ መድሃኒቶችን ለመለየት፣ ለዕቅድ ግብዓትና ለውሳኔም እንደሚያግዛቸው ነው የገለፁት።

ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ፣ ጋንዲ መታሰቢያ፣ ጥሩነሽ ቤጂንግና አይደር ሪፈራል ሆስፒታሎች ቴክኖሎጂውን በመተግበራቸው ፈጣን አገልግሎት መስጠት አስችሏቸዋል።

እንደ አቶ ኢዮብ ገለጻ ቴክኖሎጂውን በ2010 ዓ.ም በሌሎች 70 ሆስፒታሎችና 100 ጤና ጣቢያዎች ለመተግበር የኮምፒውተሮችና ሰርቨሮች ግዥ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።

እስከ 2012 ዓ.ም ድረስም በአገሪቱ የሚገኙ 400 ሆስፒታሎችና 3 ሺህ 500 ጤና ጣቢያዎችን የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተጨማሪ በ2010 ዓ.ም መጨረሻ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ሁሉንም የጤና ተቋማት በኔትወርክ ለማገናኘት ዝግጅት እየተደረገ ነው።

የጤና ተቋማቱ በኔትወርክ መገናኘት ሪፖርታቸውን በወቅቱ ለማዕከል ለመላክ፣ በታካሚዎች ዝውውር ወይም ሪፈር ወቅትም ትክክለኛ መረጃ ለመጋራት እንደሚያስችላቸው አክለዋል።

በቅርቡ 60 ሆስፒታሎችን የቴሌ-ራዲዮሎጂ መሳሪያዎች ከሚገኙባቸው ሰባት የህክምና ማዕከላት ጋር በኔትወርክ በማገናኘትና በጨረራ የመረጃ ግንኙነት መረብ በመታገዝ መስጠት የተጀመረው የህክምና አገልግሎት ውጤታማ መሆኑንም አቶ ኢዮብ ጨምረው ገልፀዋል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በጤና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከያዛቸው አራት ዋና ዋና አጀንዳዎች መካከል አንዱ ቴክኖሎጂን መጠቀም ላይ የሚያተኩረው የመረጃ አብዮት ነው።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ