አርዕስተ ዜና

ደክዊድ የተሰኘው አረም ለዶሮና ለቁም ከብት ምርታማነት አመርቂ ውጤት ታይቶበታል-ጥናት Featured

31 Aug 2017
2576 times

አዲስ አበባ ነሐሴ 25/2009 ደክዊድ የተባለው የአረም አይነት የዶሮና የቁም እንስሳት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዳ  አመርቂ ውጤት ማስገኘቱ ተገለጸ።

ጥናቱ የተከናወነው በአምቦ ዩኒቨርሲቲ እና ለተጎዱ የሚቆምበተሰኘ ድርጅት ትብብር ነው። 

የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ምስጋናው ኢቲቻ እንደገለፁት የአረም አይነቱን የተመገቡ ዶሮዎችና እና የቁም ከብቶች በእንቁላል፣ በስጋ እና ወተት ምርታቸው ውጤታማ ሆነው ተገኝተዋል።

ምርምሩ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተሞክሮ በአርሶ አደሩ ዘንድ ተቀባይነት እያገኘ መሆኑን አቶ ምስጋናው አስታውቀዋል።

የጆርጂያ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ባገኘው ውጤት መሰረት በእርግዝና ወቅት እናቶች አረሙን በመመገባቸው የህፃናት ሞትን መቀነሱ በመረጋገጡ በሌላው ክፍለ አለም ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተገልጿል ።

ጥናቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ  በአገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆን ጥረት እንደሚደረግም አቶ ምስጋናው ገልፀዋል።

በቀጣይም ከኦሮሚያ ክልል በተጨማሪ በአማራ እና በደቡብ ብሎም በመላው የሀገሪቷ ክፍሎች የዚህን የአረም አይነት ጥቅም የማስተዋወቅ ስራ እንደሚከናወንም አቶ ምስጋናው ጠቁመዋል።

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ብዙነሽ ሚደቅሳ በበኩላቸው  አረሙ ከተጠቀሰው ጥቅሙ በተጨማሪ የዶሮ እና የከብት መኖ ፍጆታን በ30 በመቶ ይቀንሳል ብለዋል።

በምርምር የተገኘውን የአረም አይነት የተጠቀሙ ዶሮዎችና የቁም ከብቶች የስጋቸው የፕሮቲን መጠን ከመደበኛው የላቀ ነው ተብሏል።

በዓሳ ልማት ላይም ጥናቱ እየተከናወነ መሆኑን ዶክተር ብዙነሽ አስረድተዋል።

አምቦ ዩኒቨርሲቲ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ጥናቶች ማካሄዱን እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። 

የአሜሪካ ተራዶኦ ድርጅት( ዩ. ኤስ. አይዲ )እና በአሜሪካን የሚገኘው ጆርጂያ ዩኒቨርሲቲ ለጥናቱ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል።

“ለተጎዱ የሚቆም” ድርጅት የህፃናት " የአካባቢ " የንፁህ መጠጥ ውሃ እና የወጣቶች ስራ ፈጠራ ልማት ላይ ድጋፍ የሚያደርግ ለትርፍ ያልተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ