አርዕስተ ዜና

የኢትዮ-ቴሌኮም የሰሜን አዲስ አበባ ሪጅን አገልግሎት አሰጣጡን እንዲያሻሽል ተጠየቀ

ፍቼ ጥር 26/2010 የኢትዮ-ቴሌኮም የሰሜን አዲስ አበባ ሪጅን የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ህብረተሰቡን ለማርካት ጠንክሮ እንዲሰራ በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ደንበኞች ጠየቁ ።

ሪጅኑ የአገልግሎት አሰጣጡን ማሻሻል በሚችልበት ሁኔታ ላይ ከዞኑ 13 ወረዳ ተወካዮች፣ ከፍቼ ከተማ ደንበኞችና የሥራ አጋሮቹ ጋር በፍቼ ከተማ ተወያይቷል። 

በውይይቱ ላይ ደንበኞች እንዳሉት  የኢንተርኔት፣ የፋክስ፣ የስልክ መስመር ብልሽትና ጥራት መጓደል ሲያጋጥም ፈጥኖ አለማስተካከል፣ የአገልግሎት ሒሳብ ክፍያን  በጊዜው አለመሰብሰብ፣ መረጃ ሲጠየቁ  ፈጥኖ አለመስጠትና ሌሎች መሰል ችግሮች በሪጅኑ በኩል እንደሚስተዋሉ አመልክተዋል።

ከደንበኞች  መካከል የወረጃርሶ ወረዳ አስተደደር ተወካይ አቶ ተሾመ በላይ ሪጅኑ ብዙ መመላለስ ሳይኖር ቅሬታን በአግባቡ የማስተናገድ ባህልን በማጎልበት ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ  ቀልጣፋና ፍጣን አገልግሎት ሊሰጥ እንደሚገበ ገልጸዋል ።

“በገጠር አካባቢዎች የአርሶ አደሩን  አቅም ያገናዘበ  የሞባይል  ቀፎ፣ የመደበኛ ስልክና የኢንተርኔት  አገልገሎትን ተደራሽ  በማድረግ በኩል ያለበትን ውሱንነት  በማስወገድ ጠንክሮ ሊሰራ ይገባል” ብለዋል ።

የደገም ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ተወካይ  አቶ በላይ አበበ  በበኩላቸው  ሪጅኑ ህብረተሰቡን የዘመናዊ ቴክኖሎጂና የመረጃ ተጠቃሚ ለማድረግ በየጊዜው የሚያከናውናቸው የመሰረተ ልማት ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልፀዋል ።

የኢንተርኔት አገልግሎት ተማሪውን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ስለሚያደርገው የስርጭት ጥራቱን በማስተካከል በትምህርት ተቋማት ተደራሽ ለመሆን ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም  አመልክተዋል።

 “ደንበኛው ያልተገለገለበትን  ክፍያ እንዲከፍሉ መጠየቅ፣ ብልሽት ሲገጥም ቶሎ አለመጠገን፣ የኢንተርኔትና የፋክስ መቆራረጥና መጥፋት ሊስተካከሉ የሚገባቸው የሪጅኑ ችግሮች ናቸው” ያሉት ደግሞ የፍቼ ከተማ ነዋሪ አቶ ውብሸት ጎቤ ናቸው።

ሪጅኑ የሚሰጣቸው ልዩ ልዩ አገልግሎቶች ፍትሃዊና በእኩልነት ላይ የተመሰረቱ  ሊሆን እንደሚገባም  አሳስበዋል ።

በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የኢትዮ-ቴሌኮም ተወካይ አቶ ግሩም መርሻ በበኩላቸው ከተለያዩ የልማት አጋሮች ጋር በቅንጅት በመስራት የሕብረተሰቡን ፍላጎትና ጥያቄ  ለመመለስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል  ።

ተገልጋዩ የሚገጥሙት ችግሮች በአጭር ጊዜ የሚፈቱበትን ዘመናዊ አሰራሮች በሚገባ አውቆ  አለመንቀሳቀስ እንዲሁም ለሚፈቱ ችግሮች 994 በመደወል ብቻ ረጅም ጉዞ መፍጀት ከተስተዋሉ ችግሮች  መካከል መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ይህን ለማስወገድ  የግንዛቤ መድረክ እንደሚዘጋጅ ጠቁመው የመብራት መቆራረጥ  ከኢትዮ  ቴሌኮም አገልግሎት አሰጣጥ ጋር  እንዳይገናኝ  በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን  ጠቁመዋል።

የሰሜን አዲስ አበባ ሪጅን ዋና ዳሬክተር አቶ አረዳ ጋሪ በበኩላቸው፣  ከደንበኞች  የቀረቡት  አብዛኞቹ  ቅሬታዎች  ትክክል መሆናቸውን አምነው፣ “ውይይቱ የተዘጋጀበት ዋና ዓላማ የሕዝብን  ቅሬታን  ተቀብሎ  አሰራርን ለማሻሻል ነው” ብለዋል ።

በዞኑ በኢትዮ - ቴሌኮም የሚሰጡ የተለያዩ አገልግሎቶች ለህዝብ በጥራት እንዲደርሱና አቅርቦታቸውም በእጥፍ እንዲያድግ  በቀጣይ የማስተካከያ ሥራዎች እንደሚሰሩም ገልጸዋል ።

በውይይቱ ከዞኑ 13 ወረዳዎችና  ከተሞች የተውጣጡ 250 የመንግስት፣ የግልና በሕብረተሰቡ ተሰሚነት ያላቸው ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡

Last modified on Saturday, 03 February 2018 14:47
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን