አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

በምርምር የተገኙ የሰብል ዝርያዎችን መልቀቁን የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት አስታወቀ።

03 Aug 2017
1858 times

ባህር ዳር ሀምሌ 27/2009 በአማራ ክልል የአርሶአደሩን የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ለመፍታት በምርምር የተገኙ የሰብል ዝርያዎችን መልቀቁን የክልሉ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት አስታወቀ። 

የኢኒስቲትዩቱ የሰብል ልማት ዳይሬክተር አቶ ፍቅረማርያም አሳርገው እንደገለጹት፣ አዲስ የተለቀቁት የሰብል ዝርያዎች ከስድስት እስከ ስምንት ዓመት ምርምር ሲደረግባቸው የቆዩ ናቸው።

በኢንስቲትዩቱ ስር ከሚገኙ አራት የግብርና ምርምር ማዕከላት የተለቀቁት የጤፍ፣ ማሽላ፣ ቦሎቄ ፣ አተር ፣ የምግብ ገብስና የነጭ አዝሙድ ዝርያዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል።

አቶ ፍቅረማርያም እንዳሉት ዝርያዎቹ በአነስተኛ እርጥበት በሽታና ድርቅን ተቋቁመው ፈጥነው በመድረስ በሄክታር ከ22 እስከ 47 ኩንታል ምርት መስጠት ይችላሉ።

ከአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የተለቀቀውና "ሕብር-1" የሚል ስያሜ የተሰጠው ነጭ ጤፍ በሄክታር 25 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችል ነው።

ምርታማነቱ በአካባቢው ከሚገኘው ዝርያ በ11 ነጥብ 7 ኩንታል ብልጫ ያለው ሲሆን፣ ከሰቆጣ ዞን በስተቀር በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ላለው አየር ንብረት ተስማሚ መሆኑን አስረድተዋል።

ከስሪንቃ ግብርና ምርምር ማዕከል የተገኘውና "አለነ" የሚል ስያሜ የተሰጠው የማሽላ ዝርያም ምርታማነቱ በሄክታር 47 ነጥብ 2 ኩንታል መሆኑን አመልክተዋል።

ከአካባቢው ዝርያ በ19 ኩንታል ብልጫ እንዳለውና ፈጥኖ እንደሚደረስ የገለጹት አቶ ፍቅረማርያም፣ ዝርያው እንደቆቦ፣ ጨፋና ሌሎች ተመሳሳይ እርጥበት አጠር ለሆኑ ወረዳዎች ተስማሚ መሆኑን አስታውቀዋል።

"የዋግ-ነሽ" የሚል ስያሜ የተሰጠውና ከሰቆጣ ግብርና ምርምር ማዕከል የተለቀቀው የአተር ዝርያም በሄክታር 22 ነጥብ 9 ኩንታል ምርት መስጠት እንደሚችል ተመልክቷል።

አሁን በአካባቢው ካለው የአተር ዝርያ በሄክታር በ10 ነጥብ 3 ኩንታል ብልጫ ያለው ሲሆን ለሰሜን ወሎ፣ ለዋግ-ህምራና ተመሳሳይ የአየር ፀባይ ላላቸው አካባቢዎች ተስማሚ መሆኑን አስረድተዋል።

በሁሉም ገብስ አብቃይ በሆኑ የክልሉ ደጋማ ወረዳዎች ተስማሚ እንደሆነ የተነገረለት "ደባርቅ-1" የተባለው አዲሱ የገብስ ዝርያም ኢኒስቲትዩት በምርምር ካገኛቸው የሚጠቀስ ነው። 

በሄክታር ከ22 እስከ 25 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችሉ ሁለት አዲስ የነጭ አዝሙድ ዝርያዎችም ከጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል መገኘታቸውንም ጠቁመዋል።

አቶ ፍቅረማርያም እንዳሉት፣ በብሔራዊ ዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ ፀድቀው የተለቀቁት የሰብል ዝርያዎችን በተያዘው የመኽር እርሻ በአርሶአደሩ ማሳ ላይ በማላመድ ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ዘራቸውን የማሰራጨት ሥራ ይጀመራል።

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ኢንስቲትዩቱ 250 የሰብል ዝርያዎች በምርምር በማውጣትና በማላመድ የአርሶደሩን የዘር አቅርቦት ዕጥረት ለማቃለል አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ኢንስቲትዩቱ በስሩ በሚገኙ የምርምር ማዕከላት 69 አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን በምርምር በማውጣት ወደአርሶአደሩ እንዲገቡ ማድረጉን የዘገበው ኢዜአ ነው።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ