አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

መንግስት ለቅድመ ሰው ቅሪተ አካል ምርምር ትኩረት ሊሰጥ ይገባል - ተመራማሪዎች Featured

02 Aug 2017
1945 times

አዲስ አበባ ሐምሌ 26/2009 መንግስት የቅድመ ሰው ቅሪተ አካል የምርምር ማዕከላትንና አስፈላጊ መሳሪያዎችን   በማሟላት ረገድ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ኢትዮጵያውያን የዘርፉ ተመራማሪዎች ጠየቁ።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የሰነበተው ስድስተኛው የምስራቅ አፍሪካ የቅድመ ሰው ቅሪተ አካል ጥናትና ምርምር ባለሙያዎች ማህበር ጉባኤ ዛሬ ተጠናቋል።

የኢዜአ ሪፖርተር የጉባኤው ተሳታፊ  ኢትዮጵያውያን የቅድመ ሰው ቅሪተ አካል ተመራማሪዎችን በዘርፉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ዙሪያ አነጋግሯል። 

የሰላም ቅሪተ አካልን ያገኙት ተመራማሪ ፕሮፈሰር ዘረሰናይ አለምሰገድ እንደገለጹት በቅድመ ሰው ቅሪተ አካል ጥናቶች የተገኙ ቅሪተ አካላትን ለመንከባከብ የሚያስችሉ መሳሪዎች ውስን ናቸው።

አሁን ያሉት መሳሪያዎች በአገሪቷ የሚገኙ ቅሪተ አካላት ምርምርና እንክብካቤ ለማድረግ በቂ እንዳልሆኑ ገልጸው መንግስት በዚህ ረገድ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል። 

በጀርመን ቱቢንገን ዩኒቨርስቲ የቅድመ ሰው ቅሪተ አካል ተመራማሪው ዶክተር ዮናታን ሳህሌ በኢትዮጵያ በዘርፉ ለሚደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎች የሚውሉ ማዕከላትን መገንባት ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል።

በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ምርምር በማድረግ የተገኙ ቅሪተ አካላትን የሚያከማቹና ለቀጣይ ጥናትና ምርምር ዝግጁ የሚያደርጉ ማዕከላት ግንባታ በስፋት መከናወን እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት።

በሄብሪው ዩኒቨርሲቲ የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙት አቶ ተገኑ ጎሳ በበኩላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ በዘርፉ በሚደረጉ ምርምሮች የሚገኙ ቅሪተ አካላት እየጨመሩ መምጣታቸውንና ለነዚህም የሚሆን ቦታ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በቅሪተ አካላት ላይ በሚደረጉ ምርምሮች የድንጋይ ቁሳቁስ፣ የሰውና የእንስሳት ቅሪት አካላት በቁፋሮ በስፋት እየተገኙ እንደሆነም አስረድተዋል።

ለእነዚህ ቅሪተ አካላትና ቅርሶች ማስቀመጫ የሚሆን የመሰረተ ልማት ግንባታ እንደሚያስፈልግና መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንዳለበትም ነው የጠቆሙት፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና እንክባካቤ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ እንዳሉት በቅድመ ሰው ቅሪተ አካል ላይ ለሚደረግ የጥናትና ምርምር ተግባር የሚውሉ ማዕከላት ግንባታና መሳሪያዎችን የማሟላት ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል።

በባለስልጣኑ ግቢ ውስጥ የሰው፣የእንስሳትና የእጽዋት ቅሪተ አካል ምርምር ማከናወኛ ቤተ ሙከራ ተገንብቶ  ስራ ላይ መዋሉንም ገልጸዋል።

ቤተ ሙከራው ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሌሎች አገራት ተመራማሪዎች ለሚያደርጓቸው የጥናት ምርምር ስራዎች በማዕከልነት እያገለገለ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

የቤተ ሙከራው መገንባት በቂ እንዳልሆነ ገልጸው የሰው ዘር አመጣጥ ሙዝየም ለመገንባት የዲዛይን ስራ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

የሚገነባው ሙዝየም ቅሪተ አካላትን ከማሰባሰብ ባለፈ የምርምርና ጥናት ስራዎች የሚከናወኑበት እንደሚሆን ነው አቶ ዮናስ ያብራሩት።

ቅሪተ አካሉ ደህንነቱ እንዲረጋገጥ የሚያደርገው የሲቲ ስካን ማሽንና ሌሎች ለምርምርና እንክብካቤ የሚያገለግሉ መሳሪዎች በቤተ ሙከራው እንደሚገኙም ገልጸዋል።

በ 2009 ዓ.ም ለዘርፉ የሚያስፈልጉ ሌሎች መሳሪያዎች ግዢ እንደተከናወነ አስታውሰው መሳሪያዎቹ በአሁኑ ወቅት በቤተ ሙከራው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

የመሳሪያዎቹ ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ ከግዥ ይልቅ  በውሰት የመጠቀም ስራ መካሄዱንም ተናግረዋል።  

ኢትዮጵያ በቅሪተ አካል ምርምርና ቅድመ ታሪክ ጥናት ከ12 በላይ ቅሪተ አካላት ተገኝተውባታል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ