አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የሲናና ግብርና ምርምር አምስት የሰብልና የጥራጥሬ ዝሪያዎችን መልቀቁን አስታወቀ

02 Aug 2017
1565 times

ጎባ ሐምሌ 26/2009 የሲናና ግብርና ምርምር ማእከል በምርምር ያገኘቸው አምስት የሰብልና የጥራጥሬ ዝሪያዎች መልቀቁን አስታወቀ፡፡

የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ በሪሶ ለኢዜአ እንደገለጹት በምርምር የተገኙት እነዚሁ ዝርያዎች በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የስንዴ፣ አጃ፣ ባቄላና አተር ዝርያዎች ናቸው፡፡

በብሔራዊ የዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ ከታዩ በኋላ ከተለቀቁት ዝርያዎች መካከል ”ቡላላ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የፖስታና ማካሮኒ ስንዴ የቢጫ ዋግ በሽታን ተቋቁሞ በሄክታር እስከ 55 ኩንታል ምርት ይሰጣል፡፡

የስንዴ ዝርያው የተሻለ ምርት ከመስጠት ባሻገር ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡

 “ሆርቱ”ና “ዌይብ” የሚል ሰያሜ የተሰጣቸው የአተር ዝሪያዎች ደግሞ በሄክታር ከ50 እስከ 55 ኩንታል፤  “አሎሼ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የባቄላ ዝርያ ደግሞ በሄክታር ከ35 እስከ 40 ኩንታል ምርት ይሰጣል፡፡

እንዲሁም  “ሀይደሮ “ የሚል ስያሜ የተሰጠው  የአጃ ዝርያ በሄክታር ከ42 እስከ 50 ኩንታል ምርት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

በምርምር የተገኙት የሰብልና የጥራጥሬ ዝሪያዎች በአርሶ አደሩ እጅ ከሚገኙ ዝርያዎች ከ15 እስከ 20 በመቶ የምርት ጭማሪ የሚያስገኙ ናቸው፡፡

ምርጥ ዝርያዎቹን አባዝቶ ለአርሶ አደሩ ለማድረስ  ምርጥ ዘር ከሚያባዙ ኢንተርፕራይዞች፣ በየደረጃው ከሚገኙ የግብርና ጽህፈት ቤቶችና አርሶ አደሮች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑም ተናግረዋል፡፡ 

የኦሮሚያ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ የባሌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረወልድ ኪዳኔ በበኩላቸው ኢንተርፕራይዙ ከሲናና ግብርና ምርምር ማዕከልና ከሌሎች የምርምር ማዕከላት የወጡ የተሻሻሉ የሰብል ዝሪያዎችን በመቀበል እያባዛ በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሩና በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላት እያደረሰ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል በ1978 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ዘንድሮ የተለቀቁትን ሳይጨምር በብዕር፣ አገዳና በፍራፍሬ እንዲሁም በእንስሳት መኖ ላይ ያተኮሩ ከ57 በላይ የምርምር ውጤቶችን ለተጠቃሚው ማድረሱን ከማዕከሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ