አርዕስተ ዜና

የወልድያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ እያስገነባ ነው

18 Jun 2017
2445 times

ወልዲያ ሰኔ 11/2009 የወልድያ ዩኒቨርሲቲ በ8 ሚሊዮን ብር ወጪ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ እያስገነባ ነው።

በዩኒቨርሲቲው የሕዝብና የውጭ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኪዳነ ማርያም ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለጹት ሰሜን ወሎ ዞን ካለው ተፈጥሯዊ አቀማመጥ አስቸጋሪነት የተነሳ የሬዲዮ ስርጭት በተገቢው መንገድ እየደረሰ አይደለም፡: 

ይህንን ችግር ለመፍታትና የመረጃ ተደራሽነትን ለማስፋት ዩኒቨርሲቲው አማራጭ ሬዲዮ ጣቢያ ለመክፈት በግንባታ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም በአንድ ነባር ህንፃ ላይ የማስተላለፊያ አንቴናዎችንና አስፈላጊ ማሽኖች ተከላ እየተካሄደ ሲሆን ስራው እስከ ነሐሴ ወር ተጠናቆ በመጪው መስከረም ወር ስርጭት ይጀምራል፡፡

ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያው በ89 ነጥብ 2 ሜጋ ሄርዝ ላይ የሚተላለፍ ሲሆን ለስርጭቱ ህጋዊ ፈቃድ መያዙንም ተናግረዋል፡፡

ስርጭቱ 150 ኪሎ ሜትር ራዲየስ የሚሸፍን ሲሆን ስራውን የሚያከናውኑ 60 በጎ ፈቃደኞች የተመለመሉ ሲሆን ቋሚ ሰራተኞችን ለመቅጠር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የዞኑ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ልባሴ አሊጋዝ በበኩላቸው ሰሜን ወሎ ዞን ተራራና ሸለቆ የሚበዛበት በመሆኑ ከባህር ዳርም ሆነ ከደሴ የሚተላለፉ የሬዲዮ ስርጭቶች በአግባቡ ስለማይሰሙ የጣቢያው መከፈት ለዞኑ ህብረተሰብ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በመልካም አስተዳደርና በሌሎች ዘርፎች ወቅታዊ መረጃዎችንና የመንግስትን አቋም ለህብረተሰቡ ለማድረስ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ውል ለመፈራረም መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ