አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

የአዳማ ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ የውሃ ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ ነው Featured

17 Jun 2017
2432 times

አዳማ ሰኔ 10/2009 ሃገሪቱ ያላትን ሰፊ የውሃ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ  የውሃ ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ  መሆኑን  የአዳማ ሣይንስና  ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ አስታወቀ።

በእስራኤል የውሃ አጠቃቀም ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በዩኒቨርስቲው ተካሂዷል።

የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተሾመ አብዶ  እንደገለጹት ኢትዮጵያ ሰፊ የውሃ ሀብት ቢኖራትም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በተገቢው ተጠቃሚ አልሆነችም፡፡

የውሃ ሀብቱን በአግባቡ እንዳትጠቀም ካደረጓት ማነቆዎች መካከል የፋይናንስና የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት፣ደካማ የውሃ ሀብት አስተዳደር በዋናነት ጠቅሰዋል።

ሀገሪቱ ያላትን የውሃ ሀብት በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል መንግስት የውሃ አስተዳደር ፖሊሲ፣ስትራቴጂና የልማት ፕሮግራም በመቅረፅ ለተግባራዊነቱ በየደረጃው እየሰራ መሆኑን  አመልክተዋል።

ዩኒቨርስቲውም ይህንን  ለመደገፍ  የውሃ ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል።

ዶክተር ተሾመ እንዳሉት በአሁኑ ወቅትም  በውሃ ቴክኖሎጂ የዳበረ ልምድ ካላቸው አገራት ጋር በመተባበር ለመስራት ጥረት ተጀምሯል።

" በዘርፉ ስኬታማ ከሆኑ የዓለም አገራት መካከል እስራኤል ቀዳሚ ናት " ያሉት ዶክተር ተሾመ አውደ ጥናቱ የተዘጋጀውም  በአገሪቱ  እየተሰራበት ያለውን የውሃ አጠቃቀም ቴክኖሎጂ ምንነት እንዲሁም ከዩኒቨርስቲው የውሃ ሀብትና መስኖ የልህቀት ማዕከል ጋር ያለውን ግንኙነት በመፈተሽ አብሮ ለመስራት ታስቦ መሆኑን አመልክተዋል።

እንዲሁም በሀገሪቱ የውሃ አጠቃቀም ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ፣ውሃን በቁጠባ ለመስኖ፣ለኃይል አቅርቦት፣ለኢንዱስትሪና ለሌሎችም አገልግሎቶች ለማዋል የሚቻልበት ዘዴና  ልምድ  ለመቅሰም መሆኑንም ጠቁመዋል።

በዩኒቨርስቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ስፔሻል  ዲን ዶክተር ዘላለም ብሩ በበኩላቸው ዩኒቨርሰቲው ወጣት ተመራማሪዎችን በማፍራት የቴክኖሎጂ አቅም ለማሳደግ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል፡፡

ትናንት በተካሄደው አውደ ጥናት  በውሃ አጠቃቀም ረገድ  የእስራኤልን  ውጤታማ ቴክኖሎጂዎች  ከእስራኤል የመጡ  ከፍተኛ ባለሙያዎች ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ  ላይ የዩኒቨርስቲው ምሁራንና ባለድርሻ አካላት መክረዋል።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ