አርዕስተ ዜና

በምስራቅ ኢትዮጵያ ጥንታዊ መኖሪያ ማግኘታቸውን ተመራማሪዎች ይፋ አደረጉ

17 Jun 2017
2509 times

ሰኔ 10/2009 መሬት ውስጥ የተቀበሩ ታሪካዊ ቅርሶችን የሚያጠኑ የእንግሊዝ ተመራማሪዎች በምስራቅ ኢትዮጵያ ሃርላ አጠገብ የ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጥንታዊ ከተማ ቅሪት ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ጥናቱ የተካሄደው በአካባቢው ጥንታዊ ከተማ እንደነበር የሚያወሱ አፈ ታሪኮችን መነሻ በማድረግ ሲሆን ጥናቱም የአፈ ታሪኩን እውነታነት አረጋግጧል፡
500 በ1000 የሆነው መኖሪያ ከታላላቅ ድንጋዮች የተገነባ ግድግዳና ጣሪያ እንዳለው በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡

ከተገኙ ቅሪተ አካላት መካከልም መስጂድ፣ የእስልምና መካነ መቃብሮችና ከመቃብሩ ላይ የሚቀመጡ ምልክቶች (ለህድ) እንዲሁም  የህንድ ጌጣጌጦች ይገኙበታል፡፡

አጥኚዎቹ በቀጠናው ያገኙት ጥንታዊ የእስልምና እምነት ተከታዮች መኖሪያ በአፍሪካ የእስልምና አመጣጥ ታሪክ ላይ አዲስ ብርሃን ይፈነጥቃል የሚል እምነት አሳድሮባቸዋል፡፡

የጥናቱ መሪ በደቡብ ምዕራብ እንግሊዝ የኤክሰተር ዩኑቨርሲቲ ፕሮፌሰር ቲሞቲ ኢንሶል ግኝቱ “በአርኪዮሎጂ ጥናት ቦታ ያልተሰጠው የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ አስተሳሰባችንን ቀይሮታል” ብለዋል- አካባቢው የንግድ ማዕከል እንደነበር መረጋገጡን በመጠቆም፡፡

የ12ኛውን መቶ ክፍለ ዘመን መስጂድ ጨምሮ የእስልምና መካነ መቃብሮችና ከደንጋይ የተሰሩ የቀብር ምልክቶች፣ የብርጭቆ ስብርባሪዎች ከዓለት የተሰሩ መስታወቶች፣ ዶቃዎችና መሰል ቁሳቁሶች እንዲሁም ከማዳጋስካር፣ ከማልዲቭ፣ የመንና ቻይና የገቡ ዛጎሎችና የሸክላ ውጤቶችም በቁፋሮው ተገኝተዋል፡፡

የ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከብርና ከነሀስ የተሰሩ የግብጽ ሳንቲሞችን ማግኘታቸውንም ተመራማሪዎቹ ይፋ አድርገዋል፡፡

አጥኚዎቹ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ለሁለት ዓመታት ጥናት ያደረጉ ሲሆን ግኝቶቹ ለአካባቢው ማህበረሰብ የገቢ ማስገኛ እንዲሆኑ ለእይታ ይበቃሉም ተብሏል፡፡

 

ምንጭ፡-dailymail.co.uk

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ