አርዕስተ ዜና

በዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ሥራዎች የማህበረሰቡን ችግር እየፈቱ መሆናቸው ተጠቆመ Featured

13 May 2017
2483 times

ደብረ ብርሃን ግንቦት 5/2009 በሀገሪቱ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ወደ ማህበረሰቡ ወርደው ችግር እንዲፈቱ እየተደረገ መሆኑን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ አራተኛው ዓለም አቀፍ የምርምር ሲፖዚየም "ምርምርና ፈጠራ ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ቃል በደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ለሦስት ቀናት ተካሂዷል።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንደገለጹት፣ በሀገሪቱ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ከተጀመሩ ከ70 ዓመታት በላይ ቢቆጠርም ምርምሮቹ ለማህበረሰቡ ችግር መፍቻ ይውሉ እንዳልነበር አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄዱ የምርምር ሥራዎች በቁጥር እያደጉ መምጣታቸውን ጠቁመው፣ የጥናትና ምርምር ውጤቶች  በተግባር የህዝብን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍታት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በአንኮበር አካባቢ የጀመረው የባህላዊ መድኃኒት ጥናትና ምርምር እንዲሁም በሸዋሮቢት አካባቢ የአርሶአደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ያካሄደውን ጥናት በአብነት አንስተዋል።

በተጨማሪም "የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ በጉና ተራራ አካባቢ የአርሶአደሩን ችግር ለመፍታት የገብስና የበቅሎ ዝርያን በማሻሻል ያካሄዳቸው ምርምሮች አርሶአደሩን ተጠቃሚ ማድረግ ጀምረዋል" ብለዋል።

ከፍተኛ ገንዘብና እውቀት ፈሶባቸው የሚካሄዱ የምርምር ሥራዎች የሕብረተሰቡን ችግሮች መፍታት እንዲችሉና የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የምርምር ግኝቶችን ፈጥነው ወደ ተግባር ለማሸጋገር የጥናትና ምርምር ምክር ቤቶችን ከማቋቋም ባለፈ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።  

የደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት ደክተር አልማዝ አፈራ በበኩላቸው፣ ባለፉት ዓመታት ዩኒቨርሲቲዉ የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ጥናትና ምርምሮችን ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጸዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን በድርቅ ተጋላጭ በሆነው ሸዋ ሮቢት ወረዳ በአሳ ማርባት ባካሄደዉ ምርምር 10 ሰዎች የምግብ ዋስትናቸዉን እንዲያረጋግጡ መደረጋቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የኢኮኖሚ ችግር ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን  በጓሮ አትክልትና  በዶሮ እርባታ እንዲሁም የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸዉ ላለባቸዉ የማህበረሰብ ክፍሎች የሻማ ማምረቻ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲው በምርምር በማውጣት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ነው የገለጹት።

በአንኮበር የተጀመረው የባህላዊ መድኃኒት ምርምር ከፍተኛ ዉጤት የተገኘበት መሆኑን ጠቁመዉ፣ ወደ ተግባር ያልተሸጋገሩ ነገር ግን  ለትግበራ የተዘጋጁ  ተጨማሪ የምርምር ውጤቶች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

የምርምር ውጤቶቹ የእዉቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ የሚተገበሩ ሲሆን የሕብረተሰቡን የገቢ ምንጭ ለማሳደግ ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ዶክተር አልማዝ አመልክተዋል። 

እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ በየዓመቱ በዩኒቨርሲቲው የሚካሄደዉ የጥናትና ምርምር ሲፖዚየም የወጣት ተመራማሪዎችን ፍላጎት በማሳደግ በኩል መልካም ተሞክሮ ተገኝቶበታል።

የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸዉ ተፈራ በበኩላቸው የምርምር ሲፖዚየሙ የሀገር ውስጥ ዩኒቨርሲዎችን በተለያዩ አገራት ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ጋር በማገናኘት የምርምር ባህልን ለማዳበር ያግዛል ብለዋል።

በለፉት ዓመታተ በተካሄደ የጥናትና ምርምር ሲፖዚየም የተገኙት ተሞክሮዎችን በመቀመር ዩንቨርሲቲዉ ለሚያካሂዳቸው የማህበረሰብ አቀፍ ጥናቶች ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማግኘቱንም አስታውቀዋል።

ከሲፖዚየሙ ተሳታፊዎች መካከል በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ መምህር ይርጋለም አለሙ በበኩላቸው እንደገለጹት፣ የሚካሄዱት ጥናትና ምርምሮች የህብረተሰቡን ችግር ከመፍታት ባለፈ የሀገርን ፖሊሲ ለመቅረጽ ፋይዳቸው ከፈተኛ ነው።

ለሦስት ቀናት በተካሄደው ሲምፖዚየም ከ500 በላይ ምሁራን ተሳታፊ ሲሆኑ ከዉጪ ሀገር የመጡ ምሁራን ልምዳቸዉን ለአገር ውስጥ ተመራማሪዎች ማካፈላቸው ተገልጿል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ