አርዕስተ ዜና

ሴት ምሁራን ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ምርምሮች ላይ ማተኮር አለባቸው ተባለ

21 Apr 2017
1543 times

አዲስ አበባ ሚያዝያ 13/2009 ሴት ምሁራን ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ እንዲያተኩሩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡

ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ሴት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመተባበር ለሁለት ቀናት የሚቆይ አውደጥናት አዘጋጅቷል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንደተናገሩት ሴት ምሁራን በመኖሪያቸውና የስራ አካባቢዎቻቸው ያሉ ወጣት ሴቶችን ተደራሽና ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች በመስራት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡

ተደራሽ፣ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉና ትርጉምና ፋይዳቸው የጎላ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ላይ እንዲያተኩሩ ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያሳሰቡት፡፡

ሴቶች ሳይንስና ቴክኖሎጂን በህብረተሰቡ ዘንድ ማስረጽና ማህበራዊ ችግሮችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መፍታት የሚያስችል አቅም ማዳበር እንዳለባቸው ተናግረው ምሁራኑ እስከ ቀበሌ ድረስ ባለው መንግስታዊ መዋቅር ካሉ የሴቶች ጉዳይ ቢሮዎች ጋር መስራት እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው መዋቅራዊ ለውጥ የሴቶችን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተደራሽነትና ተጠቃሚነት ከግምት ያስገባ መሆኑን ያስታወሱት ፕሮፌሰር አፈወርቅ የቴክኖሎጂ አቅም ክምችትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሴት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ማህበርም አባላቱ አገር አቀፍ በሆኑ ትልልቅና ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር ላይ እንዲሰሩ ማበረታታት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር የዓለምፀሀይ መኮንን በበኩላቸው ማህበሩ በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ወጣት ሴት ምሁራን በራሳቸው የሚተማመኑና የላቀ ምሁራዊ አስተዋፆ የሚያበረክቱ እንዲሆኑ የማበረታታትና አዳዲስ ዕድሎችን የማመቻቸት ስራ እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ከተመሰረተ ሦስት ዓመታትን ያስቆጠረው ማህበሩ ብዙ መስራት የሚጠበቅበት ቢሆንም አባላቱ የሚያገኙትን ማንኛውንም ድጋፍ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

ይሁንና በኢንዱስትሪዎች፣ በምርምር ተቋማትና ሌሎች የሳይንስ ዘርፎች የሚሰሩ የሴት ተመራማሪዎችና ምሁራን ቁጥር አሁንም በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ሚኒስቴሩ ይህን ችግር ለመፍታት አሰራር ዘርግቶ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ ለተሰማሩ ሴቶች የተለያዩ የማበረታቻ ሽልማቶችንና ድጋፎችን ሲያደርገ መቆየቱ ይታወሳል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ