አርዕስተ ዜና
×

Warning

JUser: :_load: Unable to load user with ID: 452

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን ታዘጋጃለች Featured

21 Apr 2017
1609 times

አዲስ አበባ ሚያዝያ 13/2009 ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን ለማካሄድ ዝግጅት ላይ መሆኗን የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በአገር አቀፍ ደረጃ የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን ላለፉት ዘጠኝ አመታት ሲዘጋጅ በዘርፉ የሚሰሩ የግልና የመንግስት ተቋማት መካከል የልምድ ልውውጥ ከመፈጠሩም ባሻገር የገበያ ትስስርና ሌሎች ውጤቶች መገኘታቸው ተገልጿል።

የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታቸው ነጋሽ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን /አይ ሲ ቲ አክስፖ/ ስታዘጋጅ የመጀመሪያዋ ነው።

ሚኒስትር ዴኤታው በውጭ የሚገኙ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የውጭ ኩባንያዎች በኤግዚቢሽኑ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት አላቸው፤ ይህም ጥሩ አጋጣሚ ነው ብለዋል።

የኤግዚቢሽኑ ቀዳሚ ዓላማ የአይ ሲ ቲ ተጠቃሚነትንና አገልግሎትን ማሳደግ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

በአገሪቱ በንግድ ተቋማት፣ በኤጀንሲዎች፣ በመንግስት ተቋማትና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ውስጥ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና ተሞክሮዎችን ማስተዋወቅም የዓላማው አካል ነው።

የአገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤቶች፣ ተመራማሪዎች እንዲሁም ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ግኝቶቻቸውን እንዲያስተዋውቁና ከዓለም አቀፍና አገር አቀፍ መሰል ተቋማት ጋር ትስስር የሚያደርጉበት መድረክ መፍጠርም እንዲሁ።

ኤግዚቢሽኑ የልምድ ልውውጥና የገበያ ትስስሩን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ በማድረግ የአገር ውስጥ ድርጅቶች ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በመስራት ተሞክሯቸውን ለማሳደግ እንደሚረዳም ተናግረዋል።

በተለይም የትምህርት፣ የጤና፣ የግብርናና የፋይናንሱን ዘርፍ ዲጂታል ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት መደላድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

በዘርፉ ያለውን ንግድና ኢንቨስትመንት በማስፋት የሶፍትዌርና ሃርድዌር ኩባንያ ለመክፈት ፍላጎት ላላቸው የአገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ዕድል እንደሚፈጥርና የአገሪቱን የማምረቻ ዘርፍ ዕድገት እንደሚያፋጥንም ተናግረዋል።

የቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽኑ ከሰኔ 21 እስከ 25 ቀን 2009 ዓም "ዲጂታል ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል በሚሌኒየም አዳራሽ የሚካሄድ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ጉብኝት፣ ጉባኤዎች፣ የጥያቄና መልስ ፕሮግራምና የገበያ ትስስር መድረኮች እንደሚኖሩም ታውቋል።

በፕሮግራሙ ላይ የሶፍትዌርና ሃርድዌር ኩባንያዎች፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት፣ የመንግስት ተቋማት፣ ጥቃቅንና አነስተኛ እንዲሁም ጀማሪ የአይሲቲ ድርጅቶችና አገልግሎት ሰጪዎችን ጨምሮ ከ100 በላይ በዘርፉ የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ