አርዕስተ ዜና

በክልሉ የግብርና ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ማምረት የሚችል ህብረተሰብ ለመፍጠር እየተሰራ ነው

20 Apr 2017
1532 times

ሚያዝያ 11/2009 በአማራ ክልል ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትን ተደራሽ በማድረግ የግብርና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ማምረት የሚችል ህብረተሰብ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የጎልማሶች መደበኛ ያልሆነና የማህበረሰብ ልማት ትምህርት ኬዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ማረው ደርሶ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በዘንድሮ ዓመት ከአንድ ሚሊዮን 622 ሺህ በላይ ጎልማሶች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ይገኛሉ።

ይህም በበጀት ዓመቱ በዕቅድ ከተያዘው ጋር ሲነጻጸር 64 ነጥብ አምስት በመቶ ያህል መሆኑን ጠቁመው፣ በቀሪ ጊዜያት ሁሉም ጎልማሶች እንዲማሩ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ትምህርቱን ለመስጠት ከ15 ሺህ በላይ ነባርና አዲስ የመማሪያ ጣቢያዎችና በዘርፉ የሰለጠኑ 27 ሺህ 481 አመቻቾች መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ፣ በየአካባቢው የሚገኙ የጤና፣ የትምህርትና የግብርና ባለሙያዎች ትምህርቱን በመስጠት ላይ ናቸው።

ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርትን በመጠናከር ቴክኖሎጂን ፈጥኖ በመቀበል ሕይወቱን መለወጥ የሚችል ማህበረሰብ ለመፍጠር ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ትምህርቱ ከተጀመረበት ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2008ዓ.ም ድረስ ሦስት ሚሊዮን 66 ሺህ ጎልማሶች ማንበብ፣ መጻፍና ቁጥር ማስላት በመቻላቸው ተመርቀዋል።

ተመራቂ አርሶ አደሮች በበኩላቸው መማራቸው ሳይንሳዊ አሰራርን በመከተልና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ የግብርና ሥራ በማከናወን የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

በባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ ወንዳጣ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ እማዋይሽ በላይ “ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ተከታትዬ ስመረቅ ከጨለማ ወደ ብርሃን እንደተሸጋገርኩ ነው የተሰማኝ” ብለዋል። 

በመማራቸው ያገኙት እውቀት የግልና የአካባቢ ንፅህናቸውን በመጠበቅና የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ ከራሳቸው ባለፈ የቤተሰባቸው ጤንነት እንዲጠብቅ ያገዛቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ ወቅቶች የሚያከናውኑት የግብርና ሥራም ዘመናው የእርሻ ስራን የተከተለ መሆኑን አመልክተዋል።

በእዚሁ ወረዳ የሚኖሩት አርሶአደር አድማሱ ጥላሁን በበኩላቸው ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ከመማራቸው በፊት የግብርና ስራቸውን ያከናውኑ የነበረው በዘልማድ የግብርና አሰራር ነበር።

ከ2006 ዓ.ም በኋላ ትምህርቱን አጠናቀው በመመረቃቸው ለእርሻ ሥራቸው ማዳበሪያና ምርጥ ዘርን በአግባቡ በመጠቀም እያለሙ መሆናቸውንና በእዚህም የተሻለ ውጤት እያገኙ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

የማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣን በ2004 ዓ.ም ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው በአማራ ክልል ከአምስት ሚሊዮን 761 ሺህ በላይ ያልተማሩ ሰዎች ይገኛሉ።

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ