አርዕስተ ዜና

የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ የአየር ብክለትን የሚከላከል አዲስ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ አዋለ Featured

19 Apr 2017
1971 times

 መቀሌ ሚያዚያ 11/2009 የመሰቦ  ሲሚንቶ ፋብሪካ  የአየር ብክለትን የሚከላከል አዲስ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ማዋሉን አስታወቀ።

 ቀደም ሲል ፋብሪካው በካይ የአፈር ብናኝን ወደ ከባቢ አየር በመልቀቅ በአየር ንብረት ላይ ተፅዕኖ ያስከትል የነበረው አሰራር በአዲስ ቴክኖሎጂ መተካት ችሏል።

 በፋብሪካው የፕሮጀክቶች አስተባባሪ አቶ ሳሙኤል ነጋሽ ትናንት ለኢዜአ እንደገለፁት፣ ፋብሪካው በሰዓት  አምስት ቶን የአፈር ብናኝ  ወደ ከባቢ አየር በመልቀቅ ችግር ሲያስከትል ቆይቷዋል።

 "ብናኙ በአካባቢው በሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖሪያ ቤት፣በእንስሳት ግጠሽና መጠጥ ውሀ ላይ እያረፈ ችግር ያስከትል ነበር "ብለዋል፡፡

 ብናኙን  ለመቆጣጠርና መልሶ  ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ ከሁለት ሳምንት በፊት አገልግሎት ላይ ማዋላቸውን አስተባባሪው አስታውቀዋል፡፡

 ቴክኖሎጂው በመስፍን ኢንዳስትሪያል ኢንጂነሪንግና በአንድ የቻይና ተቋራጭ የተሰራ ሲሆን፣፣ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡

 ቴክኖሎጂው ወደ ከባቢ አየር ይለቀው የነበረውን የአፈር ብናኝ አፍኖ ከማስቀረቱ በተጨማሪም መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚያደርግ ነው፡፡

 አቶ ሳሙኤል እንዳመለከቱት በተጨማሪም ፋብሪካው የስሚንቶ ግብአትን ለማምረት ሲጠቀምበት የነበረውና አከባቢውን የሚረብሽው የደማሚት ፍንዳታ  ድምፅ መቀነስም ተችሏል፡፡

 ፋብሪው ከሚጠቀምበት ንፁህ ውሀ ተጣርቶ ወደ አርሶ አደሮች መንደር ይለቀቅ የነበረው ጨዋማ ውሀም በአንድ ጉድጓድ እንዲጠራቀም በማድረግ ብክለቱን መቆጣጠር መቻሉንም ጠቁመዋል።

 ኢዜአ ያነጋገራቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች ግን ፋብሪካው የአፈር ብናኙ በመቆጠጣጠሩ የተወሰነ እፎይታ እንዳስገኘላቸው ገልጸዋል፡፡

 በፋብሪካው አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደር አያሌው ሀይሉ "ብናኙ በመኖሪያ ቤት፣በግጦሽና በወራጅ ወንዝ ላይ እያረፈ በሰውና እንስሳት ጤና ላይ ችግር ያደርስብን ነበር "ብለዋል፡፡

 አሁን ፋብሪካው የጀመረው የአፈር ብናኙን የመቆጣጠር ስራ ዘላቂ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡

 ሆኖም ግን የስሚንቶ መጥበሻ ከሚጠቀሙበት የድንጋይ ከሰል በክረምት ወቅት ከፋብሪከው ታጥቦ ወደ ወንዝና ሰብላቸው የሚፈስ በመሆኑ  ውሀውን የመበከልና  ሰብልም የማቃጠል ችግር እያስከተለባቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

 አርሶ አደር ካሕሱ አለማየሁ በበኩላቸው፣ፋብሪካው ተራራውን ለማፍረስ ይጠቀሙበት የነበረው የደማሚት ድምፅ አሁን የቀነሰ ቢሆንም አልፎ አልፎ ሌሊት እንደሚረብሻቸውም አመልክተዋል፡፡

 በፋብሪካው የፕሮጀክቶች አስተባባሪ አቶ ሳሙኤል ነጋሽ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ፣ ሲሚንቶ ለመጥበስ የሚጠቀሙበት የከሰል ድንጋይ በሌላ  ለመተካት እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

 ይሄውም  ዘንድሮ 13 በመቶ ያህል የሰሊጥ ተረፈ ምርት ጥቅም ላይ ማዋላቸውን ጠቅሰው፣ በቀጣዩ ዘመንም  ወደ 40 በመቶ ለማድረስ ማቀዳቸውንም ጠቁመዋል፡፡

 በአካባቢው የሚገኙ የሰሊጥና ሌሎች ተረፈ ምርት በመጠቀም የከሰል ድንጋይ የአገልግሎት ድርሻ ዝቅ በማድረግ የህብረተሰቡን ቅሬታ በዘላቂነት ለመፍታት ጥረቱ  ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቅሰዋል፡፡

 የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከመቀሌ ከተማ ወጣ ብሎ የሚገኝ ነው፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ