አርዕስተ ዜና

ጎግል ጎጂ ይዘት ያላቸውን 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ማስታወቂያዎችን ማስወገዱን ገለፀ

መጋቢት 5/2010 ግዙፉ የኢንተርኔት ኩባንያ ይህን እርምጃ የወሰደው በፈረንጆቹ 2017 ሲሆን ከ2016 ጋር ሲነፃፀርም የወሰደው እርምጃ በ88 በመቶ መጨመሩን ጠቁሟል።

ጎግል በ2016 ብቻ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ጎጂ ማስታዎቂያዎች በመባል የሚጠራቸውን መረጃዎች አየር ላይ እንዳይውሉ ማድረጉ ይታወቃል።

ባለፈው ዓመት ደግሞ በአንድ ሰከንድ በአማካይ 100 ጎጂ ማስታዎቂያዎች እንዳይሰራጩ የማድረግ ስራ ሰርቷል።

ጎግል መጥፎ ወይም ጎጂ ማስታዎቂያዎች የሚላቸው መረጃን ለመጥለፍ፣ ገንዘብ ማጭበርበር፣ እና የኮምፒውተር ቫይረስ ለመልቀቅ ዓላማ የተሰሩ ሲሆኑ የኩባንያውን የማስታወቂያ ፖሊሲ የጣሱ መሆናቸውንም ገልጿል።

አሁን ላይ መጥፎ ማስታዎቂያዎች በጎግል የኢንተርኔት መቃኛ ተሰራጭተው በህብረተሰቡ በተለይም በተጠቃሚዎች ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት የመከላከል ስራውን እያጠናከረ እንደሚገኝም ነው የጠቆመው።

ኩባንያው በዚህ ስራው ከፖሊሲው ጋር የማይስማሙ 320 ሺህ የኢንተርኔት ማስታዎቂያ አታሚ ድረ-ገጾችን ከመረጃ መረቡ ተጠቃሚነት አስወግዷል።

ሌሎች 90 ሺህ ድረ-ገጾችን እና 700 ሺህ የሞባይል መተግበሪያዎችን ደግሞ ስጋት የሚፈጥሩ በሚል በጥቁር መዝገብ አስፍሯቸዋል።

ጎግል እስካሁን ካስወገዳቸው ጎጂ ማስታዎቂያዎች መካከል አብዛኛዎቹ የኢንተርኔት መቃኛ ተጠቃሚዎችን ያለፍላጎታቸው ሳቢና አስገዳጅ የማስፈንጠሪያ ስርዓቶችን በመጠቀም ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ናቸው ብሏል።

በ2017 የጎግል ፖሊሲ በመጣሳቸው ምክንያት በየወሩ 2 ሚሊየን የመጠቀሚያ ገጾች ተሰርዘዋል።

ኩባንያው ጎግል ታማኝ የመረጃ ምንጭና የመልዕክት መለዋወጫ እንዲሁም የማስታወቂያ አገልግሎት ሰጪ መሆኑን ለማስቀጠል የጎጂ ማስታወቂያዎችን እገዳ በማጠናከር ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።

ምንጭ፡-venturebeat.com

 

Last modified on Saturday, 17 March 2018 21:40
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን