አርዕስተ ዜና

በምስራቅ አማራ የተሻሻሉ የበቆሎ ምርጥ ዘሮች በመጪው መኸር ጥቅም ላይ ሊውሉ ነው

11 Mar 2017
1544 times

ደሴ መጋቢት 2/2009 የላቀ የምግብ ይዘት ያላቸውና የተሻለ ምርት የሚሰጡ የበቆሎ ምርጥ ዘሮችን በመጪው የመኸር ወቅት ጥቅም ላይ እንደሚያውል የአማራ ክልል ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ አስታወቀ።

ኢንተርፕራይዙ ከክልሉ ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር በምስራቅ አማራ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር አዲስ በወጡ የበቆሎ ምርጥ ዘሮች ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

በኢንተርፕራይዙ የዘር ጥራትና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ደምለው አበበ ትላንት በደሴ ከተማ በተደረገው ውይይት ላይ እንደገለፁት ምርጥ ዘሩ መልካሳ 6 ኪው፣ ኤም ኤች 138 ኪውና ቢ ኤች ኪው ፒ ዋይ 545 የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ናቸው።

እርጥበት አጠር ለሆኑት የምስራቅ አማራ አካባቢዎች የሚስማሙና ድርቅን ተቋቁመው ከ120 እስከ 145 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ ለምርት እንደሚደርሱ በጥናት መረጋገጡንም ተናግረዋል።

በተለምዶ ከሚመረተው የበቆሎ ዝርያ በሄክታር የሚገኘውን 15 ኩንታል ከአራት እጥፍ በላይ ከማሳደጋቸውም ባለፈ በተሻለ የምግብ ይዘታቸው በክልሉ ህፃናት ላይ የሚስተዋለውን የመቀንጨርና የመቀጨጭ ችግር እንደሚያቃልሉም ተናግረዋል።

በአርሶ አደሩና በባለሙያው ዘንድ በምርጥ ዘሮቹ ላይ ግንዛቤ ከተፈጠረ በኋላ በምስራቅ አማራ አምስት ዞኖች ውስጥ በጥናት በተለዩ 12 ወረዳዎች  አንድ ሺህ 425 ኩንታል ዘር ለማሰራጨት ከወዲሁ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል

በመጭው መኽር  የሚሰራጩት ምርጥ ዘሮች አምስት ሺህ 700 ሄክታር መሬት እንደሚያለሙ የገለፁት አቶ ደምለው ከሚለማው መሬት በአማካይ 205 ሺህ 200 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አመልክተዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግሥቴ በበኩላቸው ቢ ኤች 545 የተባለ ምርጥ ዘር በምእራብ አማራ ለሚገኙ በቆሎ አምራች አርሶ አደሮች ተሰራጭቶ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ውጤታማ እንደነበር አስታውሰዋል ።

ክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመቀንጨር ችግር ከተጠቁ ክልሎች ግንባር ቀደም መሆኑን ያወሱት ምክትል ቢሮ ኃላፊው አዲስ የተዋወቁት ምርጥ ዘሮች የምግብ ይዘታቸው ከፍተኛ መሆን ችግሩን ለማቃለል አስተዋጽዖ እንዳለው ተናግረዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን የላስታ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብል ልማትና ጥበቃ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሰለሞን ብርሃነመስቀል በበኩላቸው እንደገለጹት አዲስ የተገኙት የበቆሎ ምርጥ ዘሮች የአርሶ አደሩን ምርታማነት የሚያሳድጉ ናቸው።

"ወረዳው ዝናብ አጠርና በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቃ በመሆኑ ምርጥ ዘሮቹ የአርሶ አደሩን ምርታማነትና የሰብሉን የምግብ ይዘት ለማሳደግ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል” ብለዋል።

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ