አርዕስተ ዜና

በትግራይ ክልል 26 የፈጠራ ባለሙያዎች ተሸለሙ

12 Feb 2017
1818 times

መቀሌ የካቲት 5/2009 በትግራይ ክልል በፈጠራ ስራዎቻቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ 26 የፈጠራ ባለሙያዎች ትናንት የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት ተበረከተላቸው፡፡

ሽልማቱ ለላቀ ስራ እንዲነሳሱ መንገድ እንደፈጠረላቸው ተሸላሚዎች ገልጸዋል።

የፈጠራ ባለሙያዎቹ ለሽልማት የበቁት ለእርሻ ልማት፣ ለማኑፋክቸሪግ፣ ለአካል ጉዳተኞች የሚጠቅሙና ለሌሎች የልማት ዘርፎች  አጋዥ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ፈጥረው ለአገልግሎት በማብቃታቸው መሆኑን የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብርሃ ኪሮስ ገልፀዋል፡፡

ከፈጠራ ባለሙያዎች በተጨማሪም በፈጠራ ስራ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ያልተቋረጠ ድጋፍ ያደረጉ ሁለት የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ባለሙያዎችም የሽልማቱ ተቋዳሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ለፈጠራ ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪዎች ከቢሮው የተዘጋጀ ከ5 ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር ሽልማት እንደተበረከተላቸው ዶክተር አብርሃ ገልፀዋል፡፡

ወጣት አያና ታደለ በትግራይ ምዕራባዊ ዞን ቃፍታ ሁመራ ወረዳ ነዋሪ ሲሆን በእለቱ የማበረታቻ ሽልማት ከተበረከተላቸው  መካከል አንዱ ነው፡፡

ወጣት አያና የሰሊጥ ምርትን በማጨድ፣ በመሰብሰብ፣ በመውቃትና በማጣራት በሰዓት 20 ኩንታል ምርት የሚያዘጋጅ ማሽን ሰርቶ ለአገልግሎት አብቅቷል።

ወጣቱ የሰራው ማሽን ለተጠቃሚ አርሶ አደሮች በ12 ሺህ ብር በማቅረብ ላይ መሆኑን ገልፆ ዋጋው ከውጭ ከሚገባው ማሽን ጋር ሲነጻጸር  ዝቅተኛ መሆኑን ተናግሯል።

ወጣት አያና የአርሶ አደሩን ችግር ፈቺ ማሽን በመስራቱ ከክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ የተዘጋጀለትን 10 ሺህ ብር ሽልማት ተቀብሏል።

ሽልማቱ ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመስራት አቅም እንደሚሆነው በስነስርዓቱ ላይ ተናግሯል።

ከሶስተኛ ክፍል ያለፈ የቀለም ትምህርት እንደሌላቸው የተናገሩት  የዓድዋ ከተማ ነዋሪ አቶ አረጋዊ በላይ በበኩላቸው በአንድ ሰዓት ውስጥ ከ10 ኩንታል በላይ የእንስሳት ድርቆሽ ፈጭቶ የሚያዘጋጅ ዘመናዊ ማሽን ሰርተው ለአገልግሎት ማብቃታቸውን ተናግረዋል።

''በክልሉ መንግስት እውቅና አግኝቼ የስድስት ሺህ ብር ተሸላሚ በመሆኔ ሌላ የፈጠራ ውጤት ለማቅረብ ተዘጋጅቻለሁ '' ብለዋል።

የክልሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮን በመምራት፣ ሰርተው በማሰራት አርአያ ናቸው የተባሉት ዶክተር ከላሊ አድሀና  ደግሞ የ10 ሺህ ብር የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

ሽልማቱ ወደፊት ለላቀ የፈጠራ ስራና ተጨማሪ ኃላፊነት እንዲነሳሱ መንገድ እንደከፈተላቸው ተናግረዋል።

በፈጠራ ስራ ለተሰማሩ ባለሙያዎች መንግስት የማያቋርጥ ድጋፍ ካደረገላቸው በርግጠኝነት የኢንዳስትሪ ልማት ስትራቴጂው ሊያፋጥኑ የሚችሉና ደረጃቸውን የጠበቁ የፈጠራ ውጤቶች ሊሰሩ እንደሚችሉ ዶክተር ከላሊ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል ።

የወጣቶችን የፈጠራ ውጤት ገበያና እውቅና እንዲያገኝ በማገዝና በማስተዋወቅ ያልተቆጠበ ጥረት አድርገዋል ተብለው የ10 ሺህ ብር ሽልማት የተሰጣቸው ደግሞ የቢሮው ባለሙያ ዶክተር መኮነን ሀይለስላሴ ናቸው።

ለፈጠራ ባለሙያዎች የተዘጋጀውን የገንዘብ ሽልማት የሰጡት የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደርና የክልሉ የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ አምባሳደር ዶክተር አዲስ አለም ባሌማ ናቸው።

ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ''በተለያዩ የፈጠራ ስራዎች ተሰማርተው ራሳቸውንና ህዝባቸውን የሚጠቅሙ ባለሙያዎችን ለማበረታታት የክልሉ መንግስት ሁሌም ዝግጁ ነው'' ብለዋል።

 

 

 

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ