አርዕስተ ዜና

የፈጠራ ውጤቶቻቸውን ለማሳደግ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የፈጠራ ባለቤቶች ተናገሩ

07 Feb 2017
1340 times

መቀሌ ጥር 30/2009 የፈጠራ ውጤቶቻቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ  ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በመቀሌ ከተማ የሚገኙ ሶስት የፈጠራ ባለቤቶች ተናገሩ፡፡

የፈጠራ ባለቤቶቹ ለኢዜአ እንደገለጹት መንግስት ለፈጠራ ውጤቶች ተገቢ ድጋፍ ባለመደረጉ  ስራዎቻቸውን ወደ ተጠቃሚዎች ዘልቀው ሊገቡ አልቻሉምል፡፡

በመቀሌ  ዩኒቨርስቲ የሶፍት ዌር ኢንጅነሪንግ መምህር ፈረደ ዓሊ ከሙያ ጓዳኞቻቸው ጋር በመሆኑን የመንግስት ንብረትና ሀብት ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለማስተዳደር የሚያችል ሶፍትዌር በመፍጠር  ለአገልግሎት አብቅተዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ለአገልግሎት ያበቁት ይህው ስራ ከክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ  የእውቅና ማረጋገጫ ሰርትፊኬት  አግኝቷል።

" ሶፍትዌሩ እያንዳንዱ የመንግስት ንብረትና ሀብት በስርዓት መያዙና አለመያዙን በግልፅ ያሳያል " ያሉት የፈጠራው ባለቤት የሶፍትዌሩ ሲስተም ለመግዛት እስከ 50 ሚሊዮን ብር የሚጠይቅ መሆኑን  አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ከ70 የሚበልጡ የመንግስት ተቋማት ለአንድ ዓመት በነፃ እንዲጠቀሙበት ከክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚያዊ ልማት ቢሮ ጋር መፈራረማቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የመንግስት ድጋፍና ቁርጠኝነት ካለ  ከሀገሪቱ  አልፎ በዓለም ገበያ  የሚቀርብ  የፈጠራ ውጤት በተፈለገው ፍጥነትና ጥራት ማቅረብ የሚችሉ ወጣቶች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

ሌላው  የፈጠራ ባለቤት  ወጣት ክብሮም ሀፍቱ በበኩሉ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር ምክንያት የእግር አካል ጉዳት ላጋጠማቸው  ወገኖች በእጅ የሚሰራ የሽመና መሳሪያ ሰርቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን ገልጿል፡፡

ወጣቱ በተጨማሪም ሶስት ሜትር ይረዝም የነበረው የቀድመው የሽመና መሳሪያ አሁን ወደ አንድ ሜትር ዝቅ እንዲል ማድረግ ችሏል፡፡

" መሳሪያው ለስራ ቀላል ከማድረጉ በተጨማሪ  የአንዱ የሽመና መሳሪያ ዋጋ ከሶስት ሺህ ብር የማይበልጥ በመሆኑ ተጠቃሚዎች በቀላሉ የሚያገኙት መሆኑ ተመራጭ ያደረገዋል"ብሏል፡፡

የወጣቱ የፈጠራ ውጤት እውቅና የተሰጠው ከመንግስትና ከግል ተቋም ሳይሆን ከቤተሰቦቹ በተደረገለት የ20ሺህ ብር ድጋፍ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ወጣቱ እስከ አሁን በክልሉ ለሚገኙ አካል ጉዳተኞች 30 የሚሆኑ የሽመና መሳሪያዎች አምርቶ እንዲጠቀሙበት አድርጓል፡፡

የመስሪያ ቦታና የፋይናንስ ድጋፍ ከተደረገለት ደግሞ በርካታ የአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራዎች ማከናወን እንደሚችል ወጣቱ ጠቁሟል፡፡

በጎርፍ መውረጃ ቱቦዎች በመግጠም ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ በመለየት የጎርፍ ፍሰቱን ጠብቆ እንዲሄድ የሚያደርግ የፈጠራ ስራ ጥቅም ላይ ያዋለው  ወጣት አሰፋ ተአምር በበኩሉ  ከክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ የእውቅና ሰርትፊኬት ማግኘቱንም ተናግሯል፡፡

የፈጠራ ውጤቱ በከተሞች የሚገኝ የጎርፍ መፋሰሻ ቱቦዎች ላይ የሚገኝ ቀዳዳ ላይ መሳሪያውን በመግጠም በራሱ ጊዜ እየተሽከረከረ ደረቅ ቆሻሻ ወደ ውጭ እንዲወጣ የሚያደርግ መሆኑን ተናግሯል፡፡

መሳሪያውን ለመስራት ሁለት አመትና ከ85ሺህ ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም የጠቆመው ወጣቱ  በመቀሌ ከተማ ጥቅም  ላይ እንዲውል  እያቀረበ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

የትግራይ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አብራሃ ኪሮስ እንደገለጹት  ቢሮው  በስምንት ዓመታት ውስጥ እውቅና የሰጣቸው የፈጠራ ባለቤቶች 150  ናቸው፡፡

የፈጠራ ውጤታቸው በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ላይ እንዲያውሉ የተደረገ ድጋፍ ቢኖርም በግልና በማህበር እየተደራጁ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያግዛቸው ድጋፍ እንዳልነበረ ጠቁመዋል፡፡

" የወጣት የፈጠራ ባለቤቶች ያለባቸውን  የገንዘብና የመስሪያ ቦታ ችግር  ከመፍታት አልፎ ክልሉን  የእውቀትና የክህሎት ገበያ ማዕከል ለማድረግ የሚያስችል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፓርክ በመቀሌ  ለመገንባት ዝግጅት እየተደረገ ነው " ብለዋል፡፡

በምርምርና በፈጠራ  ውጤታቸው አርአያ የሆኑ  28 ሰዎች  በቅርቡ የማበረታቻ ሽልማት እንደሚበረከትላቸውም ሀላፊው ጠቁመዋል፡፡

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን

 

የውጭ ምንዛሪ መቀየሪያ