አርዕስተ ዜና

የወላይታ ልማት ማህበር ያስገነባው የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ተመረቀ

ሶዶ የካቲት 26/2010 የወላይታ ልማት ማህበር ከአራት ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ያስገነባውን የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ አስመረቀ።

ሬዲዮ ጣቢያው መረጃን ተደራሽ በማድረግ ለማህበረሰቡ ሁለንተናዊ ዕድገት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አሳስቧል።

የማህበረሰብ ሬዲዮ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መሪሁን ፍቅሬ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ሬዲዮ ጣቢያው ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው ልማት ማህበሩ ከዞኑ መንግስት ጋር በመተባበር ነው።     

ሬዲዮ ጣቢያው እየተሸረሸረ የመጣውን የማህበረሰቡን ነባር ዕሴት ለማጎልበትና ለአካባቢው ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ መጎልበት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታና የልማት ማህበሩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አማኑኤል አብርሃም መንግስት መረጃ ለልማት ያለውን ፋይዳ በመረዳት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ሬዲዮ ጣቢያው የአካባቢውን የመረጃ ፍሰት በማሳለጥ በሃገር ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ ሚናውን በተገቢው መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

ህዝቡ የሚያዳምጠው ብቻ ሳይሆን የሚናገርበት የሬዲዮ ጣቢያ ሊሆን እንደሚገባም አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የፈቃድና ምዝገባ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሙሉጌታ ሲሳይ በበኩላቸው  ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ህገ መንግስታዊ መብትን በአግባቡ ለመተግበር ጥረቶች እየተደረጉ ነው፡፡

ሬዲዮ ጣቢያው መረጃን በአግባቡና በጥራት ተደራሽ በማድረግ ለማህበረሰቡ ሁለንተናዊ ዕድገት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

"የጣቢያውን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ቀሪ ግብአቶችን ማሟላትና የማህበረሰቡን ተሳትፎ ማሳደግ ይገባል" ያሉት አቶ ሙሉጌታ፣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።        

በዕለቱ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የሬዲዮ ጣቢያውን ጥራት፣ ተደራሽነትና የክህሎት ክፍተት ለመሙላትና በግብአትና በቴክኖሎጂ ሽግግር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል። 

የወላይታ ልማት ማህበር የማህበረሰብ ረዲዮ ጣቢያ "ወጌታ ኤፍ.ኤም 96.6" ከታህሳስ ወር ጀምሮ በቀን ለ7 ሰዓታት በወላይትኛና በአማርኛ ቋንቋ የሙከራ ስርጭቱን ጀምሯል፡፡

Last modified on Tuesday, 06 March 2018 00:32
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን