አርዕስተ ዜና

ደደቢት መሪነቱን ያጠናከረበትን ድል በመከላከያ ላይ አስመዘገበ

803 times

አዲስ አበባ የካቲት 6/2010  በአዲስ አበባ ስታዲየም ትናንት ማምሻውን በተደረገው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ደደቢት መከላከያን አራት ለባዶ አሸነፈ።

ጨዋታው በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ የደደቢት አጥቂ አኩዌር ቻሞ በግምት ከ25 ሜትር ርቀት ላይ ያገኘውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ከመረብ በማሳረፍ ቡድኑን መሪ አድርጎታል።

ደደቢት ግቡን ካስቆጠረ በኋላ በተደጋጋሚ ወደ መከላከያ የግብ ክልል በመድረስ ጫና መፍጠሩን ቀጥሎ በ10ኛው ደቂቃ አኩዌር ቻሞ የመከላከያን የተከላካይ ክፍል ስህተት በመጠቀም ሁለተኛውን ጎል አስቆጥሯል።

መከላከያ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ደካማ የሚባል እንቅስቃሴ በማድረጉ የፈጠራቸው የግብ ዕድሎችም አነስተኛ ናቸው።

በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ግን መከላከያ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር በማድረግ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችልም ግብ ማሰቆጠር አልቻለም።

በመጀመሪያው አጋማሽ የደደቢት አማካይ ተጫዋች አስራት መገርሳ ባጋጠመው ጉዳት በአቤል እንዳለ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያ ግብ ለማስቆጠር ተጭኖ የተጫወተ ሲሆን በአንጻሩ ደደቢት በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት ያደረገበት ነበር።

መከላከያዎች ብዙ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም በአጥቂዎች የአጨራረስ ድክመት ያገኟቸውን አጋጣሚዎች አምክነዋል።

በተለይም ሳሙኤል ታዬና ምንይሉ ወንድሙ ግብ መሆን የሚችሉ ኳሶችን አባክነዋል።

በተጨማሪም የመከላከያ የተከላካይ ክፍል በደደቢት ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ተጋላጭ ሆኖ ታይቷል።

በመልሶ ማጥቃት ሲጫወቱ የነበሩት ደደቢቶች በ81ኛው ደቂቃ በቀኝ መስመር ተጫዋቹ ስዩም ተስፋዬ ሶስተኛውን ግብ አስቆጥረዋል።

በ89ኛው ደቂቃ ሺመክት ጉግሳ ያሻገረውን ኳስ ኤፍሬም አሻሞ በአስደናቂ የአጨራረስ ብቃት ከመረብ በማሳረፍ ለደደቢት የማሳረጊያ ጎል አስቆጥሯል።

የደደቢቱ የክንፍ ተጫዋች ሺመክት ጉግሳ በጨዋታው ድንቅ ብቃቱን ማሳየት ችሏል።

ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት የመሩት ፌዴራል ዳኛ ይርጋለም ወልደጊዮርጊስ ለደደቢቶቹ ስዩም ተስፋዬና ኤፍሬም አሻሞ እንዲሁም ለመከላከያው ሺመልስ ተገኝ ቢጫ ካርድ አሳይተዋል።

የደደቢት ረዳት አሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ "በጨዋታው ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ በማድረግ የሚያስፈልገንን ሦስት ነጥብ አግኝተናል" ብለዋል።

"ወሳኝ የአጥቂ መስመር ተጫዋቾቻችንን በጉዳትና በቅጣት ብናጣም በዛሬው ጨዋታ ከሁለተኛ ቡድን ያመጣናቸው ተጫዋቾች በማጥቃት እንቅስቃሴው ውጤታማ ነበሩ" ሲሉም አክለዋል።

የመከላከያው አሰልጣኝ ምንያምር ፀጋዬ ቡድናቸው በአጠቃላይ ያደረገው እንቅስቃሴ ደካማ እንደነበርና ያገኟቸውን የግብ ዕድሎች አለመጠቀማቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግረዋል።

በውጤቱ ደስተኛ አለመሆናቸውንና ዘንድሮ ክለቡ በሊጉ እያሳየ ያለው እንቅስቃሴም ጥሩ አለመሆኑን ጠቁመዋል።

ቡድኑ ያሉበትን ችግሮች በማረም ለቀጣይ ጨዋታዎች ለማዘጋጀት እንደሚሠሩ አሰልጣኝ ምንያምር ገልጸዋል።

ደደቢት ባስመዘገበው ውጤት የሊጉን መሪነት በ28 ነጥብ ሲያጠናክር በአንፃሩ መከላከያ በነበረበት 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

መቐለ ከተማ በ25 ነጥብ ሁለተኛ፣ ጅማ አባጅፋር አዳማ ከተማና ፋሲል ከተማ በተመሳሳይ 22 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ከሦስተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

ኮከብ ግብ አግቢነቱን የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ በዘጠኝ ጎል ሲመራ፤ የአዳማ ከተማው ዳዋ ሁቴሳ የኢትዮ-ኤሌክትሪኩ ጋናዊው አል ሃሰን ካሉሻና የጅማ አባጅፋር ተጫዋች ናይጄሪያዊው ኦኪኪ አፎላቢ በተመሳሳይ ሰባት ጎሎች ይከተላሉ።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን