አርዕስተ ዜና

ድሬዳዋ ከነማ ዋልዋሎን 2 ለ 0 አሸነፈ

513 times

ድሬደዋ  የካቲት 5/2010 በድሬዳዋ ስታዲዮም ትናንት በተኪያሄደው የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ድሬ ከነማ ዋልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲን  2 ለ 0 አሸነፈ፡፡

 የድሬዳዋ ከነማ አሰልጣኝ "ለማሸነፋችን ደጋፊውና የቡድን የመንፈስ ጥንካሬ ወሳኝ ነበር " ሲሉ የዋልዋሎ አሰልጣኝ በበኩላቸው " ለሽንፈታችን ያልተገባ የዳኝነት ውሳኔ ነው " ብለዋል፡፡ 

በብዙ ሺህ የድሬ ከነማ ደጋፊዎች የታጀበው 15ኛው ሳምንት የድሬ ከነማና የዋሎዋሎ ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ቢሆንም ግብ የሚሆኑ ሙከራዎች በማድረግ በኩል ድሬ ከነማ የተሻለ ነበር፡፡

በስምንተኛው  ደቂቃ የድሬ ከነማው አክረም ኩዋሜ የመጀመሪያ ጎል ያስቆጠረ ሲሆን ግቡ ከጨዋታ ውጪ  በነበረ ተጫዋች የተቆጠረ ነው በሚል የዋልዋሎ ተጫዋቾችና አሰልጣኝ ዳኛውን ተቃውመዋል፡፡

ከእረፍት በኋላ የዋልዋሎው ብርሃኑ አሸሞ በሰራው ጥፋት በቀይ ካርድ መሰናበቱ ቡድኑ 40 ደቂቃዎችን በ10 ተጫዋቾች ጎል እንዳይቆጠርበት በመከላከል ላይ የተመሰረተ ጨዋታ ቢጫወትም በባከነ ሰዓት የድሬ ከነማው መሐመድ ጀማል ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል፡፡

ጨዋታው በድሬ ከነማ 2 ለ 0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን ለከነማ በዓመቱ ሁለተኛ ድሉ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

የድሬ ከነማ አሰልጣኝ ስምኦን አባይ በቡድኑ ተጫዋቾች ላይ የነበረውን መጨነቅ ለማስወገድ ሰፊ ሥራ መሰራቱ፣ ደጋፊ እስከ መጨረሻው ለቡድን ያደረገው ድጋፍ እንዲሁም የቡድኑን የአንድነት መንፈስ መጠናከሩ ለማሸነፍ እንዳበቃቸው ተናግረዋል፡፡

" ያገኘነውን ውጤት በቀጣይ ጨዋታ ላይ ለመድገም በጣም አስፈላጊና ወሳኝ  ይሆናል " ብለዋል፡፡

"በመጀመሪያ አካባቢ ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ጨዋታ እየተጫወቱ ነበር" ያሉት የዋልዋሎ አሰልጣኝ ሀብቶም ኪሮስ፣ "ዳኛው ከጨዋታ ውጭ የሆነ ጎል ማጽደቁና ያልተገባ ቀይ ካርድ መስጠቱ ለሽንፈታችን ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል" ብለዋል፡፡

ይህም ቢሆን ተጋጣሚያቸው በጨዋታው የተሻለ በመሆኑ ለማሸነፍ መብቃቱን ገልጸው "የዳኝነት ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል" ብለዋል፡፡

ድሬ ከነማ ማሸነፉን ተከትሎ ደረጃውን ወደ 12ተኛ ከፍ አድርጓል፡፡

Last modified on Monday, 12 February 2018 15:46
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን