አርዕስተ ዜና

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በአውሮፓ ከተሞች በተደረጉ ውድድሮች አሸንፈዋል

606 times

አዲስ አበባ  የካቲት 5/2010 ኢትዮጵጵያውያን አትሌቶች ትናንት በአውሮፓ ከተሞች በተደረጉ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ድል ቀንቷቸዋል።

በስፔን ባርሴሎና ግማሽ ማራቶንና በጣልያን ሳን ቪቶሬ ኦሎና የአገር አቋራጭ ውድድር ትናንት ማምሻውን ተካሂዷል።

በባርሴሎና የግማሽ ማራቶን ውድድር ሙሌ ዋሲሁን በ59 ደቂቃ ከ44 ሴኮንድ አሸናፊ ሆኗል። ስዊዘርላንዳዊው ጁሊየን ዋንደርስ በ60 ደቂቃ ከ00 ሴኮንድ ከ09 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ወጥቷል።

ኡጋንዳዊው ሞሰስ በ60 ደቂቃ ከ00 ሴኮንድ ከ10 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት ሶስተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቀቅ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አዝመራው መንግስቱ ሰባተኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቋል።

የውድድሩ አሸናፊ አትሌት ሙሌ በርቀቱ ያለውን የግል ምርጥ ሰአት በ16 ሴኮንድ እንዲሁም በኬንያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ ተይዞ የነበረውን የቦታውን ክብረ ወሰን በ20 ሴኮንድ ማሻሻል ችሏል።

በሴቶች ኢትዮጵያዊቷ ድባቤ ኩማ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ባህሬናዊ የሆነችውን ጠጂቱ ዳባን ተከትላ ሁለተኛ ወጥታለች። ሩዋንዳዊቷ ሳሎሜ ኒያራሩኩንዶ ሶስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

የባርሴሎና ግማሽ ማራቶን በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ የተሰጠው ውድድር ነው።

በሌላ በኩል በጣልያን ሳን ቪቶሬ ኦሎና ከተማ በተካሄደው የአገር አቋራጭ ውድድር በሴቶች የስድስት ኪሎ ሜትር ሩጫ ኢትዮጵያዊቷ ለተሰንበት ግደይ 18 ደቂቃ ከ14 ሴኮንድ በመግባት አሸናፊ ሆናለች።

አትሌቷ በመካከለኛና በአገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ ጥሩ ብቃት በማሳየት ላይ ትገኛለች።

ኬንያዊቷ ዳይሲ ጂፕኬሚ በ18 ደቂቃ ከ18 ሴኮንድ ሁለተኛ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ ሀዊ ፈይሳ በ18 ደቂቃ ከ20 ሴኮንድ ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

በሴቶቹ ባካሄዱት ውድድር ጠንካራ ፉክክር መደረጉን የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስፍሯል።

በወንዶች የ11 ኪሎ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያኖቹ አትሌቶች ሐይሌ ጥላሁንና ታዬ ግርማ ኡጋንዳዊውን ጃኮብ ኪፕሊሞን ተከትለው በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።

በጣልያን ሳን ቪቶሬ ኦሎና ከተማ ለ86ኛ ጊዜ የተካሄደው የአገር አቋራጭ ውድድር በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ፈቃድ የተሰጠው ነው።

Last modified on Monday, 12 February 2018 15:45
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን