አርዕስተ ዜና

አትሌት ዳዊት ስዩም በቦስተን የዓለም የቤት ውስጥ ውድድር አሸነፈች

734 times

አዲስ አበባ የካቲት 4/2010 አትሌት ዳዊት ስዩም በቦስተን ከተማ የተካሄደውን የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ የአንድ ሺህ 500 ሜትር ሩጫ ውድድር አሸነፈች።

ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ከሚያካሂዳቸው ስድስት ዓለም አቀፍ የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች አራተኛው ትናንት ምሽት በቦስተን ከተማ ተካሂዷል።

የመጀመሪያውና ሁለተኛው ካርልስሩህና ዱሲልዶርፍ በተባሉት የጀርመን ከተሞች፣ ሶስተኛው በስፔን መዲና ማድሪድ መካሄዱ ይታወሳል።

አትሌት ዳዊት በቦስተኑ የ1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር 04 ደቂቃ ከ04 ሴኮንድ ከ38 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት ስታሸንፍ ጃይማካዊቷ አይሻ ፕራውት 04 ደቂቃ ከ04 ሴኮንድ ከ98 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ወጥታለች።

ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳይ ጸጋይ 04 ደቂቃ ከ05 ሴኮንድ ከ91 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ ሆናለች።

በ3ሺህ ሜትር ርቀት ወንዶች ሀጎስ ገብረሕይወትና ደጀን ገብረመስቀል ኬኒያዊውን ዴቪድ ቼሴሬክን ተከትለው ሁለተኛና ሶስተኛ ወጥተዋል።

በተመሳሳይ ርቀት ሴቶች ኢትዮጵያዊቷ ፎቴን ተስፋይ ከአሜሪካዊቷ ጄኔፌር ሲምፕሰን ቀጥላ ሁለተኛ ወጥታለች። የብሪታኒያዋ ተወዳዳሪ ስቴፋኒ ትዌል ሶስተኛ በመሆን አጠናቃለች።

የፌዴሬሽኖቹ ማህበር ቀሪ ሁለት የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ውድድሮች የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም በፖላንድ ቶሩን፣ የካቲት 10 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ በስኮትላንድ ግላስኮው ከተሞች ይካሄዳሉ።

በስድስት የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ውድድሮች በየርቀቱ አጠቃላይ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች ከየካቲት 23 እስከ 25 በእንግሊዝ በርሚንግሀም ከተማ በሚካሄደው 17ኛው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በቀጥታ መሳተፋቸውን ያረጋግጣሉ።

እስካሁን በአራት ከተሞች በተካሄዱት ውድድሮች ገንዘቤ ዲባባ በ1 ሺህ 500 ሜትርና ሐጎስ ገብረሕይወት በ3 ሺህ ሜትር የተሻለ ውጤት አላቸው። በበርሚንግሀም በሚካሄደው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ለመሳተፍ ያላቸው እድል የሰፋ ነው።

በሌላ ዜና ዛሬ በጣልያን ሳን ቪቶሬ ኦሎና ከተማ በሚካሄደው 86ኛው የአገር አቋራጭ ውድድር ኢትዮጵውያን አትሌቶች ይሳተፋሉ።

ያለፈው ዓመት ውድድር የወንዶች አሸናፊው ሰለሞን ባረጋና የሴቶች አሸናፊዋ በየኑ ደገፋ የአምናውን ድላቸውን ለማስጠበቅ እንደሚሮጡ የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር በድረ ገጹ አስፍሯል።

በመካከለኛና አጭር ርቀት አስደናቂ ብቃቱን እያሳየ ያለው አትሌት ሰለሞን ከኡጋንዳዊው ጃኮብ ኪፕሊሞ ከባድ ፉክክር እንደሚጠብቀው ተገልጿል።

አትሌት ጥላሁን ኃይሌ በወንዶቹ ውድድር የሚሳተፍ ሌላው ኢትዮጵያዊ ነው።

በሴቶች ከአትሌት በየኑ ደገፋ በተጨማሪ ለተሰንበት ግደይና ሃዊ ፈይሳ ይወዳደራሉ።

በጣልያን ሳን ቪቶሬ ኦሎና ከተማ የሚካሄደው የአገር አቋራጭ ውድድር በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፈቃድና እውቅና ያለው ነው።

Last modified on Monday, 12 February 2018 15:51
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን