አርዕስተ ዜና

የአዲስ አበባ ዋንጫ የደጋፊዎችን ቀልብ በመሳብና ገቢ በማስገኘት ስኬታማ ነበር

887 times

አዲስ አበባ  የካቲት  4/2010 የደጋፊዎችን ቀልብ በመሳብና የተሻለ ገቢ በማስገኘት 12ኛው የአዲስ አበባ ዋንጫ ስኬታማ እንደነበር ተነገረ።

12ኛው የአዲስ አበባ ዋንጫ የመዝጊያና የሽልማት መርሃ ግብር  ተከናውኗል።

ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 12 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም የተካሄደው ውድድር የመዲናዋን ስድስት ክለቦች እንዲሁም ጅማ አባ ጅፋርና አዳማ ከተማን በተጋባዥነት አሳትፏል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው እንደገለጹት ውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተካሄደ ጀምሮ መሻሻል እየታየበት ነው።

የዘንድሮውም ውድድር ከሌሎቹ ዓመታት በተለየ በውድድሮች ወቅት በርካታ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም በመምጣት በከፍተኛ ድምቀት ተከናውኗል።

በተሳታፊ ክለቦች መካከል የነበረው ፉክክር ጠንካራ የሚባልና የተመልካቾችን ቀልብ የሳበም ነበር።

በሌላ በኩል ከስታዲየም ገቢ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ የተገኘ ሲሆን ይህም ከቀደሙት ዓመታት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አቶ ንጋቱ ተናግረዋል።

በ2009 ዓ.ም በተካሄደው ውድድር የተገኘውን 590 ሺህ ብር ዘንድሮ በአንድ ቀን በተካሄደ ጨዋታ ማስገባት ተችሏል ነው ያሉት።

ስፖርቱ የህዝቡ እንደመሆኑ ውድድሩን ለህብረተሰቡ ቅርብ እናድርግ በሚል ሀሳብ ከደጋፊው ጋር በመተባበር የተሰራው ስራ ውጤታማ እንደነበርና እርካታም የተገኘበት መሆኑን አንስተዋል።

የውድድሩ አዘጋጅ የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የነበሩበትን ብልሹ አሰራሮች በማረም፣ ፌዴሬሽኑን በጥሩ ሁኔታ የሚያስተዳደሩ አመራሮችን በማምጣትና በአጠቃላይ አደረጃጀቱን በአዲስ መልክ ማዋቀር መቻሉ ለውድድሩ ስኬት ተጠቃሽ ምክንያት ነው ብለዋል። 

የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጻነት ታከለ በበኩላቸው በቀጣዩ ዓመት ለሚካሄደው ውድድር ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ሁለት ክለቦችን ለማሳተፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ፌዴሬሽኑ የጀመረውን አስተዳደራዊ ዓቅም የማጠናከር ተግባር ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ በመጪው ዓመት የተሻለ ውድድር ለማዘጋጀት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በውድድሩ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ለወጡ ቡድኖች ከ500 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።

ከውድድሩ ከተሰበሰበው ገቢ በህክምና ላይ ለሚገኘው አሰልጣኝ ስዩም አባተ 10 ሺህ ብር ድጋፍ የተደረገለት ሲሆን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የ100 ሺህ ብር ቦንድ ተገዝቷል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ፣ በህክምና ላይ የሚገኘው ስዩም አባተና የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት አቶ ብርሃኑ ኃይሌ ልዩ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የ12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ ቡናን አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት በማሸነፍ ሻምፒዮን መሆኑ የሚታወስ ነው።

Last modified on Monday, 12 February 2018 15:51
Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን