አርዕስተ ዜና

የሼህ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታዲየም ለአንድ ዓመት ጨዋታ እንዳያካሂድ ታገደ

232 times

አዲሰ አበባ ሚያዝያ 8/2010 የወልዲያው የሼህ መሃመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታዲየም ለአንድ ዓመት ማንኛውንም ውድድሮች እንዳያካሂድ ታገደ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የስነ ምግባር ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት በተደረገው የ19ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ወልዲያ ከተማ ፋሲል ከተማን ባስተናገደበት ጨዋታ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች መከሰታቸው ይታወቃል።

በእለቱ በ89ኛው ደቂቃ ፋሲል ከተማ የፍጻም ቅጣት ምት ማግኘቱን ተከትሎ የወልዲያ አሰልጣኝና የወልዲያው ተጫዋች ብሩክ ቃልቦሬ  ቅጣት ምቱ እንዳይመታ ለማድረግ በመሞከራቸውና አንዳንድ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በመግባት ረብሻ እንዲፈጠርና ጨዋታው እንዲቋረጥ አድርገዋል በሚል ነው  ቅጣቱ የተላለፈው።

ይህን ተከትሎም ጨዋታ የተደረገበትን  የሼህ ሁሴን አላሙዲ ስታዲየም እስከ ሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም ድረስ ለአንድ ዓመት ያህል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሚያካሂዳቸው ማንኛቸውንም ውድድሮች እንዳያስተናግድ ውሳኔ ተላልፎበታል።

የወልዲያ ከተማ እግር ኳስ ክለብም ቀሪ ጨዋታዎችን በሙሉ ከከተማዋ 500 ኪሎ ሜትር ርቀት ባለ ሜዳ ላይ እንዲያካሂድ ተወስኖበታል።

ከዚህ በተጨማሪ የወልዲያ እግር ኳስ ክለብ  የ250 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትም እንዲከፍል ቅጣት ተላልፎበታል ።

ክለቡ በጨዋታው ወቅት በተፈጠረው ረብሻ ምክንያት የተጎዱትን የመሀል ዳኛና ረዳት ዳኛውን ሙሉ የህክምና ወጪ የሚሸፍን ይሆናል።

የወልዲያ  ከተማ አሰልጣኝ ዘማሪም ወልደጊዮርጊስ  የፍጹም ቅጣቱ እንዳይመታ ለማድረግ ወደ  ሜዳ በመግባት ለፈጠረው ችግር ለአንድ ዓመት ከአሰልጣኝነት እንዲታገድና 20 ሺህ ብር የገንዝብ ቅጣት ተላልፎበታል።

በተመሳሳይ የወልዲያ ተጫዋች የሆነው ብሩከ ቃልቦሬ ፍጹም ቅጣት ምቱ እንዳይመታና ዳኞችን ለመደብደብ ሙከራ በማድረጉ ለአንድ ዓመት ከጨዋታ የታገደ ሲሆን 10 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣትም ተላልፎበታል።

የእለቱ ውጤትም በፎርፌ ለፋሲል ከተማ እግር ኳስ ክለብ እንዲሰጥ በማድረግ ሶስት ነጥብና ሶስት ጎል እንዲያገኝ ተወስኗል።

ክለቡ ከላይ የተዘረዘሩትን ግዴታዎች ካልተወጣ  ከፕሪሚሪ ሊጉ ውድድር የሚታገድ መሆኑን ፌደሬሽኑ በጻፈው ደብዳቤ ገልጿል።

Rate this item
(1 Vote)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን