አርዕስተ ዜና

የኢትዮጵያ የቻን ውድድር ዝግጅት ሂደትን የሚገመግመው የካፍ ተቆጣጣሪ ልዑክ ዛሬ ስራውን ጀምሯል

190 times

አዲስ አበባ ሚያዝያ 8/2010 ኢትዮጵያ የአፍሪካ አገራት ዋንጫ (ቻን) ውድድሩን ለማስተናገድ ያላትን ዝግጁነት የሚገመግም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን (ካፍ) ልዑክ ዛሬ በይፋ ስራውን ጀምሯል።

ከሁለት ዓመት በኋላ የአፍሪካ አገራት ዋንጫ (ቻን) ለማስተናገድ አገሪቱ እያደረገች ያለውን ዝግጅት ለመገመገም ስድስት አባላት የያዘው የካፍ ተቆጣጣሪ ልዑክ ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብቷል።

የካፍ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው ጥር ወር 2010 ዓ.ም በሞሮኮ ካዛብላንካ ባደረገው ስብሰባ ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማስተናገድ የጀመረችውን ቅድመ ዝግጅት የሚፈትሽ ተቆጣጣሪ ልዑክ በሶስት ወራት ውስጥ እንደሚልክ አሳውቆ እንደነበር ይታወሳል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ዳንኤል ዘርአብሩክ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የካፍ ተቆጣጣሪ ልዑክ በዋነኝነት ስታዲየሞችና መሰረተ ልማቶችን ይመለከታል።

ዛሬ የአደይ አበባ ስታዲየምና በመዲናዋ የሚገኙ ሆቴሎችን እየጎበኙ መሆናቸውንና በክልል የሃዋሳ፣ መቐለና ድሬዳዋ ስታዲየሞችን  ይመለከታሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በባህርዳር፣ ሃዋሳና መቐለ እየተገነቡ ያሉት ስታዲየሞች በግንባታ ላይ እንደሚገኙና ሆኖም ውድድሩን ለማስተናገድ በሚቀሩት 20 ወራት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው ለውድድሩ ዝግጁ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

የድሬዳዋ ስታዲየም በማስፋፊያ ስራ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።

ልዑኩ በክልሉ የሚገኙ ስታዲየሞችን ከመመልከት በተጨማሪ የሆቴሎችን እንደሚገመግም ተናግረዋል።

የተቆጣጣሪው ቡድኑ እስከ ሚያዚያ 17 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቆይታ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።

መንግሥት ውድድሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲዘጋጅ የሚያስፈልጉ የሆቴሎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎትና ተዛማጅ ሥራዎችን በማከናወን  እንደሚገኝ አቶ ዳንኤል አስረድተዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ካፍ ኢትዮጵያ ውድድሩን እንድታዘጋጅ ከሁለት ዓመት በፊት እንደመረጣት ይታወሳል።

ኢትዮጵያ ባለፈው ጥር ወር 2010 ዓ.ም የ2020 የአፍሪካ አገሮች እግር ኳስ ሻምፒዮና (ቻን) ውድድር ለማዘጋጀት የውድድሩን ዓርማ  ከሞሮኮ መረከቧ ይታወሳል።

የአፍሪካ አገራት ዋንጫ(ቻን) ውድድር በአገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ነው።

Rate this item
(0 votes)

ኢዜአ ፎቶ እይታ

በማህበራዊ ድረገፅ ይጎብኙን